ኢንዱስትሪዎች ወደ አገር ውስጥ የሚያስገቧቸውን ኬሚካሎች የሚያሳውቁበት ስርዓት ተዘርግቷል - ኢዜአ አማርኛ
ኢንዱስትሪዎች ወደ አገር ውስጥ የሚያስገቧቸውን ኬሚካሎች የሚያሳውቁበት ስርዓት ተዘርግቷል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 23/2013(ኢዜአ) ኢንዱስትሪዎች ወደ አገር ውስጥ የሚያስገቧቸውን ኬሚካሎች የሚያሳውቁበት ስርዓት መዘርጋቱን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን አስታወቁ።
የተቋማቱ ሃላፊዎች ጉዳዩን አስመልክተው የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዮሀንስ ድንቅአየሁ እንደገለጹት ኬሚካሎች በመድሃኒት ዝግጅት፣ በግብርናና በኢንዱስት ግብዓትነት ዋና አንቀሳቃሽ ናቸው።
ሆኖም እነዚህ ኬሚካሎች በዘመናዊ አሰራር ተመዝግበውና ተይዘው ስለማይገኙ፣ የአገልግሎት ጊዜያቸው ማብቂያ ስለማይታወቅ የአየር ብክለትና የጤና እክል እየፈጠሩ ይገኛሉ ብለዋል።
በመሆኑም የእነዚህ ኬሚካሎች አጠቃቀም በሚገባ ታውቆ ጉዳትን በሚቀንስ ሁኔታ ሊወገዱ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ኬሚካሎች ሲገቡ ታውቀው፣ ተመዝግበው፣ መቼ እንደተመረቱና መቼ እንደሚወገዱ በዘመናዊ አሰራር ክትትል ሊደረግባቸው እንደሚገባም ገልፀዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እነዚህን ኬሚካሎች የመቆጣጠር ስልጣን እንዳለውና ድርጅቶች ወደ አገር ውስጥ የሚያስገቧቸውን ኬሚካሎችም የማሳወቅ ግዴታ እንደተጣለባቸውም አብራርተዋል።
ምንነታቸውና ከየት እንደመጡ የማይታወቁ ኬሚካሎች በሰዎችና በአየር ንብረት ላይ የሚያስከትሉትን ችግር ለማስወገድ ከዚህ ዓመት ጀምሮ ኬሚካሎችን የመመዝገብ ሂደት ይከናወናል ብለዋል።
የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወይዘሮ ፍሬነሽ መኩሪያም ኬሚካሎች ከሚሰጡት ጥቅም ባሻገር በእንስሳትና በአካባቢ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያደርሱ መታወቅ አለበት ነው ያሉት።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኬሚካሎች በሰዎች ላይ እያደረሱት ያለው ጉዳት አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ ልዩ ትኩረት ሊደረግባቸው እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ለተለያዩ አገልግሎቶች ጥቅም ላይ ሲውል የነበረው ዲዲቲ የተባለውን የፀረ ተባይ ኬሚካል ክምችት ለማስወገድ እየተደረገ ያለው ጥረት ምን ይመስላል በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ምክትል ኮሚሽነሯ ኬሚካሉ በአገር ውስጥ መወገድ ስለማይቻል ወደውጭ ለመላክ የማሸግ ስራ መጀመሩን ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ እነዚህንና መሰል ኬሚካሎችን ለማስወገድ የሚጠቀምበትን የቦታ ግንባታ በ10 ዓመት ዕቅድ ውስጥ አካቶ እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።