በመሬት የይዞታ ማረጋገጫ አሰጣጥ ላይ ለሚታዩ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት እየሰራሁ ነው... የድሬዳዋ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ - ኢዜአ አማርኛ
በመሬት የይዞታ ማረጋገጫ አሰጣጥ ላይ ለሚታዩ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት እየሰራሁ ነው... የድሬዳዋ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ
ድሬዳዋ፤ታህሳስ 22/2013/ኢዜአ/በድሬዳዋ ከተማ ከመሬት ይዞታ ማረጋገጥ ሂደት ጋር ተያይዘው ለሚነሱ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት የካዳስተር ምዝገባ ስርዓት መጀመሩን የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ አስታወቀ፡፡
በቢሮው የከተማ ይዞታ ምዝገባ መረጃ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሙና መሐመድ ለኢዜአ እንደገለፁት በድሬዳዋ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ከሚነሳባቸው ጉዳዮች መካከል ከይዞታ ማረጋገጫ አሰጣጥ ጋር የሚነሱ ችግሮች ዋናዎቹ ናቸው፡፡
የከተማ መሬት በዘመናዊ መንገድ ተመዝግቦ በመረጃ ቋት አለመመዝገቡና ለአንድ ይዞታ ለተለያዩ አካላት ካርታ መሰጠቱ ነዋሪዎችን ለቅሬታ ሲዳረጉ የቆዩ ችግሮች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ከይዞታ አሰጣጥ ጋር በወሰን አለማክበርና መሰል ችግሮች እየተነሱ አሳማኝ ባልሆኑ ምክንያቶች የካርታ መምከንም ነዋሪውን ለብሶት ዳርጎት የቆየ መሆኑን ጠቀሰዋል ፡፡
ከይዞታ አሰጣጥና ከመሬት ምዝገባ ጋር ለሚስተዋለው ስር የሰደደ ችግር ሥር ነቀል መፍትሄ ለመስጠት የካዳስተር ሥርዓት ትግበራ መጀመሩን አመልክተዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ በአዲሱ የአሰራር ሥርዓት በከተማና ቀበሌዎች በሰነድና በመረጃ የተመዘገበውን መሬት ቦታው ሄዶ በማረጋገጥ ለባለ ይዞታው የተረጋገጠ ይዞታ ይሰጣል።
የኤጀንሲው የከተማ መሬት ይዞታ መብት ምዝገባ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ዳንኤል ተረፈ በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት በመሬት ዘርፍ ላይ የምዝገባ ሥርዓት ባለመኖሩ በኢንቨስትመንት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን ተናግረዋል፡፡
"የተጀመረው የካዳስተር ስርዓት ችግሩን በመፍታት ለከተማው ማህበራዊና ምጣኔሃብት እድገት መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ያስችላል" ብለዋል፡፡
የአሰራር ሥርዓቱ የባለይዞታዎች ክርክርን ከመቀነሱም በላይ ህብረተሰቡ ዋስትናው ተረጋግጦለት ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።
የይዞታ ማረጋገጥ ስርዓት ከተጀመረ ወዲህ የአንድ ሺህ 71 ባለይዞቻዎች ይዞታ መረጋገጡንና በዘጠኙም ቀበሌዎች ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉን አመልክተዋል፡፡
በድሬዳዋ የሚገኙ ባለይዞታዎችም አዲሱ የካዳስተር የአሰራር ሥርዓት መተግበሩ ከይዞታ ማረጋገጥ ጋር ተያይዞ ለሚገጥማቸው ችግሮች መፍትሄ እንደሚያመጣ ያላቸውን ተሰፋ ገልጸዋል።
ከአስተያየት ሰጭዎቹ መካከል አቶ ሞላ ተኩዬ "የተጀመረው ዘመናዊ የይዞታ ማረጋገጫ አሰራር መልካምና ለችግሮች መፍትሄ የሚሰጥ ይሆናል ብየ አሰባለሁ" ብለዋል፡፡
"ከዚህ በፊት በነበረው ወጥነት የሌለው አሰራር በይዞታዬ ላይ ለሌላ ሰዎች ካርታ ወጥቷል፤ በዚህም የተነሳ በክርክር ላይ አገኛለሁ" ያሉት ደግሞ አቶ ሸምሰዲን አሊ ናቸው፡፡
"አዲሱ አሰራር ዘላቂ መፍትሄ እንደሚያመጣ ተረድቻለሁ፤ ለተግባራዊነቱ አስፈላጊውን ትብብር አደርጋለሁ" ብለዋል፡፡
የተጀመረው የካዳስተር ስርዓት በከንቲባው በሚመራና ከፍትህና ከፀጥታ እንዲሁም ከከተማ ማዘጋጃ ቤት የተውጣጡ አባላትን በኮሚቴነት የያዘ ሲሆን፤ ከሚቴውም በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የሚደገፍ መሆኑ ታውቋል፡፡