ቀጥታ፡

የጭነት ትራንስፖርት ኦፕሬተሮች የአደረጃጀት ብቃት ማረጋገጫና የአፈፃፀም መመሪያ ተሻሻለ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 23/2013 (ኢዜአ) የጭነት ትራንስፖርት ኦፕሬተሮች የአደረጃጀት ብቃት ማረጋገጫና የአፈፃፀም መመሪያ ተሻሽሎ መዘጋጀቱን የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን አስታውቋል።

የተሻሻለው መመሪያ በጭነት ትራንስፖርት አገልግሎት የሥራ ዘርፍ የተሰማሩ ኦፕሬተሮችን ውስጣዊ አሠራር ቀጣይነት ባለው መልኩ የሚያጠናክር ነው ተብሏል።

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ያደታ የመመሪያ ማሻሻያውን አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያን የጭነት ትራንስፖርት ዘርፍ ለማዘመንና ከዓለም አቀፍ የጭነት ትራንስፖርት ጋር ተወዳዳሪ ለማድረግ ነባሩን መመሪያ ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ መሻሻሉን ገልፀዋል።

ዘርፉ የአገሪቷን ልማት እንዲደግፍ የአደረጃጀት ብቃቱን በማሻሻል ቀልጣፋ፣ ጥራት ያለውና በዋጋ ተወዳዳሪ እንዲሆን ለማድረግም እንዲሁ።

የተሻሻለው መመሪያ የዘርፉ ደህንነት፣ ጥራትና አስተማማኝነቱ ተጠብቆ ቀጣይነት ያለው ዕድገት እንዲያስመዘግብ የሚያግዝ ነው ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ።

በተጨማሪም ግልፅና የጠራ የአደረጃጀት ሥርዓት በመዘርጋት በቴክኖሎጂ ውጤቶች የታገዘ ጠንካራና ዘመናዊ የመረጃ ልውውጥ ሥርዓት የሚከተሉ የጭነት ትራንስፖርት ኦፕሬተሮችን ለማፍራት እንደሆነም አክለዋል።

የተሻሻለው መመሪያ አዳዲስ ባለሃብቶች ወደ ዘርፉ የሚገቡበትን ሁኔታ በማመቻቸት የአገልግሎቱን ቀጣይነት እንደሚያረጋግጥ ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ከጥቅምት 16 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የሆነው መመሪያ ቁጥር 35/2013 ዓ.ም በአገር አቋራጭና በዓለም አቀፍ የንግድ መንገድ ጭነት ማመላለሻ የንግድ ሥራ የተደራጁና ፈቃድ በወሰዱ ኦፕሬተሮች ላይ ተፈፃሚ የሚሆን ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም