ቀጥታ፡

የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ ድርጊትና ውጤቱ ሠብዓዊነት ላይ ያነጣጠረ ወንጀል ተፈጽሟል - ኮሚሽኑ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 23/2013 (ኢዜአ) የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች ድርጊቱና ውጤቱ ሠብዓዊነት ላይ ያነጣጠረ ወንጀል መፈፀሙን ማረጋገጡን የኢትዮጵያ ሠብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ በኦሮሚያ ክልል 40 አካባቢዎች የአርቲስቱን ግድያ ተከትሎ በግለሰቦችና በታጠቁ የፀጥታ አካላት የተፈፀሙ የሠብዓዊ መብት ጥሰቶችን ሪፖርት ዛሬ ይፋ አድርጓል።

ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለን ጨምሮ የመብት ጥሰት ምርመራው ላይ የተሳተፉ ባለሙያዎች የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

ምርመራው በሃጫሉ ላይ ግድያው ከተፈፀመበት ጀምሮ እስከ ሶስት ቀናት ድረስ የተፈጸሙ የሠብዓዊ መብት ጥሰቶችን ያካተተ መሆኑም ተመልክቷል።

በዚሁ መሰረት በወቅቱ የመብት ጥሰቱ ሰለባ የሆኑ ግለሰቦች፣ የመንግስት አካላትና የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን አካቶ ለ328 ሰዎች ቃለ መጠይቅ ተደርጓል።

በምርመራ ሂደቱ የፎቶግራፍ፣ የድምጽ፣ የምስለ ድምጽና ሁኔታውን ሊያንጸባርቁ የሚችሉ የተለያዩ ሰነዶች መዳሰሳቸውን ተብራርቷል።

የተፈጸመውን የመብጥ ጥሰት ያብራሩት ኮሚሽነሩ ዶክተር ዳንኤል በወቅቱ ሠብዓዊነት ላይ ያነጣጠረ ወንጀል ተፈጽሟል ብለዋል።

እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ በወቅቱ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ሕይወታቸውን አጥተዋል፣ ተፈናቅለዋል፣ ንብረትም ወድሟል።

ይህም የተፈጸመው ከፊል ብሔራቸው፣ ኃይማኖታቸውና ማንነታቸው ተለይቶ ነው ብለዋል።

ውጤቱ ደግሞ ምርመራው በተካሄደባቸው 40 ከተሞች የ123 ሰዎች ሕይወት አልፏል፣ 500 ሰዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ በሺህዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ተፈናቅለዋል ብለዋል ኮሚሽነሩ።

በሰዎች ላይ የተፈጸመው ግድያ በጩቤ፣ በድንጋይ፣ በዱላና በሌሎች መሳሪያዎች የታገዘ መሆኑንም ኮሚሽኑ በምርምራው አረጋግጧል ብለዋል።

በወቅቱ የጸጥታ ኃይሎች ንጹሃንን ከመጠበቅ አንጻር በተወሰነ መልኩ ጥረት ቢያደርጉም ዳተኝነት ነበረበት በማለት አቅርበዋል።

በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ የጸጥታ ኃይሉ በወሰደው ያልተመጣጠነ እርምጃ በሰልፍ ውስጥ ያልነበሩ፣ ቤታቸው በር ላይ የነበሩ ንጹሃን የጉዳቱ ሰለባ ሆነዋል ነው ያሉት።

በጥቅሉ በኮሚሽኑ ምርመራ በተሸፈኑ አካባቢዎች ድርጊቱና ውጤቱ በሠብዓዊነት ላይ ያነጣጠረ ወንጀል መፈፀሙ እንደተረጋገጠ አብራርተዋል።

በምርመራ ሂደቱ የተሳተፉት የኮሚሽኑ ባልደረባ ዶክተር ሚዛኔ አባተ የኮሚሽኑን ምክረ ሃሳብ አቅርበዋል።

በዚህም ለተለያዩ የመንግስት አካላት የተሰጠው ምክር ሃሳብ በዋናነት በወንጀሉ የተሳተፉ አካላት ለሕግ እንዲቀርቡና ጠንካራ ስልት ሊነደፍ እንደሚገባ የተጠቆመበት ነው።

በመግለጫው መገባደጃ ከጋዜጠኞች የምርመራው ውጤት ዘግይቷል፣ የተፈጸመው ወንጀል የዘር ማጥፋት አይደለም ወይ፣ የተጠቂዎች ቁጥር ይህ ብቻ ነው ወይ? የሚሉ ጥያቄዎች ተነስተዋል።

ኮሚሽነሩ ዶክተር ዳንኤል ሲመልሱ ኮሚሽኑ ባካሄደው ምርመራ ወንጀሉ የዘር ማጥፋት አለመሆኑን ያሳያል ብለዋል።

መዘግየቱም ከተደራራቢ ስራዎች አንጻር መሆኑን ጠቅሰው የተጎጂዎች ቁጥርም ምርመራው በተካሄደባቸው 40 አካባቢዎች ብቻ የተመለከተ ነው በማለት አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም