ቀጥታ፡

በመተከል ዞን ማረሚያ ቤት በተደረገ ጉብኝት ከሁለት ዓመታት በላይ ፍርድ ቤት ያልቀረቡ ተጠርጣሪዎች ተገኙ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 23/2013 (ኢዜአ)  በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተቋቋመው የተቀናጀ ግብረ ኃይል በመተከል ዞን ማረሚያ ቤት ባደረገው ጉብኝት ከሁለት ዓመታት በላይ ፍርድ ቤት ያልቀረቡ ተጠርጣሪዎችን አገኘ።

ተጠርጣሪዎቹ ጉዳያቸው ታይቶ በሶስት ቀናት ውስጥ እልባት እንዲሰጣቸውም ግብረ ሃይሉ አሳስቧል።

ግብረ ሃይሉ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ማረሚያ ቤት ባደረገው ጉብኝት ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በነበረ የፀጥታ ችግር በወንጀል ተጠርጥረው እስካሁን ፍርድ ቤት ያልቀረቡ ተጠርጣሪዎችን አግኝቷል።

ከፀጥታ ችግር ጋር ተያይዞ በወንጀል ተጠርጥረው ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ከሁለት ዓመት በላይ በማረሚያ ቤት መቆየታቸውንም አረጋግጧል።

በግብረ ኃይሉ የህግ ማስከበርና የፀጥታውን ዘርፍ በበላይነት የሚመሩት ሌተናል ጀነራል አስራት ዴኔሮ ተጠርጣሪዎቹ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ከሁለት አመታት በላይ መታሰራቸው ከህግ አግባብ ውጭ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ተጠርጣሪዎቹ ጉዳያቸው ታይቶ በሶስት ቀናት ውስጥ እልባት ሊሰጣቸው ይገባል ብለዋል።

በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች ጉዳያቸው ታይቶ ውሳኔ እንዲያገኙና ጉዳያቸው በመረጃ ያልተረጋገጠ ተጠርጣሪዎች ደግሞ የዋስትና መብታቸው ሊከበርላቸው ይገባል ብለዋል።

በዚህም ከፌደራል ዐቃቤ ህግ መርማሪ ቡድን ጋር ስራውን የሚመራ ኮሜቴ ተቋቁሞ በሚቀጥሉት ሶስት ቀናት ወስጥ ለማጠናቀቅ እያጣራ መሆኑን ገልጸዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተቋቋመው የተቀናጀ ግብረ ኃይል በዞኑ ህግ የማስከበርና በወንጀል የተጠረጠሩ አካላት በህግ ተጠያቂ እንዲሁኑ እንዲሁም የተቸገሩ ወገኖች ሰብአዊ እርዳታ እንዲያገኙ በመስራት ላይ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም