በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማዕድን ልማት ማዕከል ተቋቋመ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማዕድን ልማት ማዕከል ተቋቋመ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 23/2013 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማዕድን ልማት ማዕከል መቋቋሙን የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ኢንጂነር ታከለ ኡማ ገለጹ።
የማዕከሉ መቋቋም የማዕድን ዘርፉን ዘመናዊትን የተላበሰ ለማድረግ አስተዋጽኦው ወሳኝ ነው ብለዋል።
ሚኒስትሩ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት በኢትዮጵያ የልጆቿን ሕይወት መቀየር የሚችሉ የከበሩ ማዕድናት በከርሰ ምድሯ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ሃብቷን በከርሰ ምድሯ አምቃ የምትኖር የጸጋዎች ምድር መሆኗንም ነው የገለጹት።
ኢንጂነር ታከለ "ልጆቿ በየትኛውም ጫፍ የሚገኙ የከርሰ ምድርም ይሁን የገጸ ምድር ሃብቶቿን መርምረው በሚገባ እንድትጠቀም በማድረግ ከትውልድ ትውልድ ያበለጽጓቷል" ብለዋል።
ለዚህም በእውቀት መደገፍ ስላለባቸው ለውጥኑ የመጀመሪያው እርምጃ "የኢትዮጵያ የማዕድን ልማት ማዕከል" በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ፋኩልቲ ስር መቋቋሙን ጠቁመዋል።
ማዕከሉ በማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ሀሳብ አመንጪነት መቋቋሙንም ጠቁመዋል።
"የማዕከሉ መቋቋም የማዕድን ዘርፉ በሚታሰበውና ወቅቱን በሚመጥን መልኩ ዘመናዊነትን እንዲላበስ ለሚደረገው ጥረት እንደ ወሳኝ እርምጃ ይቆጠራል" ብለዋል።
ለዕውቀት ማበልፀጊያ የሚሆነውን የማዕከሉ ሥራ ወጪ ሙሉ በሙሉ በማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር እንደሚሸፈን ነው ኢንጂነር ታከለ ያስረዱት።
ማዕከሉን የሚመራ ዳይሬክተር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንደሚሰየምና በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚመራ የዳይሬክተሮች ቦርድ መዋቀሩን ሚኒስትር ታከለ ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።
ቦርዱ ሰባት ዓባላት ያሉት ሲሆን በኢንጂነር ታከለ ኡማ ሰብሳቢነት እንደሚመራም ታውቋል።
የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴርና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ታሕሳስ 12 ቀን 2013 ዓ.ም መፈራረማቸው ይታወሳል።
ስምምነቱ ለ10 ዓመት የሚቆይ ሲሆን ከኢትዮጵያ ማዕድን ሀብትና ከዘርፉ ጋር የተጣጣሙ እንዲሁም በማዕድን ዘርፍ የተለዩ የእውቀት መስኮችን በመለየት በዩኒቨርሲቲው በስርዓተ ትምህርት እንዲዘጋጅላቸውና ለባለሙያዎችም እንዲሰጡ የሚያስችል ነው።
በስምምነቱ አማካኝነት በ10 ዓመት ውስጥ ከ600 በላይ ባለሙያዎች በማዕድን ዘርፍ የሚሰለጥኑ ሲሆን በተያዘው የ2013 ዓ.ም 40 ባለሙያዎች ትምህርታቸውን ይጀምራሉ ተብሏል።