ሕብረተሰቡ ኮቪድ-19 ወረርሽኝን በመከላከል እያሳየ ካለው መዘናጋት ማውጣትን ዓላማ ያደረገ የንቅናቄ ዘመቻ ሊጀመር ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሕብረተሰቡ ኮቪድ-19 ወረርሽኝን በመከላከል እያሳየ ካለው መዘናጋት ማውጣትን ዓላማ ያደረገ የንቅናቄ ዘመቻ ሊጀመር ነው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 22/2013(ኢዜአ) ሕብረተሰቡ ኮቪድ-19 ወረርሽኝን በመከላከል እያሳየ ካለው መዘናጋት ማውጣትን ዓላማ ያደረገ አገር አቀፍ ዘመቻ ሊጀመር መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
ብዙኃን መገናኛዎች በዚህ ወቅት ህብረተሰቡን ግንዛቤ ማስበጫ በመስጠትና በማንቃት ህዝባዊ ወገንተኝነታቸውን እንዲያሳዩ ተጠይቋል።
የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን የንቅናቄ ዘመቻውን አስመልክቶ ዛሬ ለመገናኛ ብዙኃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
ዘመቻው ማህበረሰቡ ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ እንዳይጋለጥ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማድረግን ጨምሮ እጅን በሳሙና መታጠብ፣ የእጅ ማጽጃ ኬሚካል(ሳኒታይዘር) መጠቀምና አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ እንዲቻል ንቅናቄ መፍጠር ላይ ያተኮረ ነው።
የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሳህረላ አብዱላሂ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ዘመቻው ሕብረተሰቡ ቀደም ሲል ኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል ሲያደረጋቸው የነበሩ የጥንቃቄ እርምጃዎችን ማስቀጠል ዓላማው አድርጓል።
ለስድስት ወር የሚቆየው ዘመቻው ሁሉም የክልል ርዕሰ መስተዳድሮች፣ የከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን የሚያሳትፍ መሆኑንም ነው የገለጹት ።
አገራዊ ዘመቻው በቀጣይ ሳምንታት ውስጥ በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ይፋ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።
ሕብረተሰቡ በተለይ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል አጠቃቀም ላይ በመላ ሀገሪቱ እየቀነሰ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ በአዲስ አበባ ከተማ 70 በመቶ የነበረው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ አጠቃቀም ከ50 በመቶም በታች መውረዱን በማሳያነት አንስተዋል።
የኮሮናቫይረስ የሚገኝባቸውና ወደ ጽኑ ህሙማን ክፍል የሚገቡ የሰዎች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መሆኑንም ገልጸዋል።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሥርጭት በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ ኢትዮጵያ ወረርሽኙን መቋቋም ወደ ማትችልበት ደረጃ እንደምትደርስም ነው ያስጠነቀቁት።
ለአገር አቀፉ የንቅናቄ ዘመቻ ስኬታማነት ብዙኃን መገናኛዎች የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡም ነው ወይዘሮ ሳህረላ ጥሪ ያቀረቡት።
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ በበኩላቸው መገናኛ ብዙኃን ሕብረተሰቡን ከመዘናጋት የመታደግ ሃላፊነት እንዳለበት ተናግረዋል።
ህብረተሰቡን ከወረርሽኙ መከላከል የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ማከናወን እንደሚገባቸው አመልክተዋል።
መጋቢት 4 ቀን 2013 ዓ.ም በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተጠቂ ከተመዘገበበት ጊዜ አንስቶ ወረርሽኙ በአገሪቷ በፍጥነት እየተዛመተ ይገኛል።
ዜናው እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ በኢትዮጵያ 123 ሺህ 856 ሰዎች በኮሮናቫይረስ የተገኘባቸው ሲሆን 1 ሺህ 918 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸው ማለፉን ከጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ከቀናት በፊት በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እያሻቀበ እንደሚገኝ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
"የራሳችንን ሕይወት እንታደግ የሌሎችንም ሕይወት እናትርፍ" ሲሉም ህብረተሰቡ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚወሰዱ የጥንቃቄ እርምጃዎችን እንዲተገብር መልዕክት አስተላልፈዋል።