የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሼር ካምፓኒ የስፖርት ጋዜጠኞችን ይቅርታ ጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሼር ካምፓኒ የስፖርት ጋዜጠኞችን ይቅርታ ጠየቀ
አዲስ አበባ ታህሳስ 22/2013 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሼር ካምፓኒ የስፖርት ጋዜጠኞችን ይቅርታ ጠየቀ።
የስፖርት ጋዜጠኞች ዘገባዎችን ለመስራት ወደ ስታዲየም ለመግባት ስንሞከር በአግባቡ አልተስተናገድንም በሚል ቅሬታ ማቅረባቸው ይታወሳል።
የጋዜጠኞቹ ቅሬታ በዋናነት ወደ ስታዲየም እንዳንገባ እንደረጋለን እንዲሁም የሚገቡት ጋዜጠኞችም ጨዋታውን ለመከታተል የሚያመች ቦታ አልተዘጋጀላቸውም የሚል ነው።
በመግለጫው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሼር ካምፓኒ ማህበር ፕሬዚዳንት መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ የዚህ ዓመት የቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ ኮቪድ- 19 ለመከላከል የወጣውን ፕሮቶኮል በጠበቀ መልኩ እንዲካሄድ የሰው ቁጥር ለመመጠን የግድ አስፈላጊ ነበር ብለዋል።
እንዲሁም የሊግ ካምፓኒው በዚህ ዓመት በዲ ኤስ ቲቪ በቴሌቪዥን ጨዋታዎችን ለማስተላለፍ ውል ተዋውሎ መስራቱ አዲስ ነገር ነው ብለዋል።
በዚህ ሂደት ከጋዜጠኞች ጋር በተያያዘ የተፈጠሩት ችግሮች ተገቢ አለመሆኑን በመግለጽ ይቅርታ ጠይቀዋል።
በቀጣይ ግን የጋዜጠኞችን ቁጥር በመመጠን በተሰጣቸው መታወቂያ እንዲገቡ ይደረጋል ብለዋል።
ለጋዜጠኞች የተዘጋጀው መግቢያ ካርድ አንዳንዶቹ ሐሰተኛ ካርዶች በመዘጋጀታቸው በቀጣይ ሌላ መታወቂያ ይዘጋጃልም ብለዋል።
የማህበሩ ፕሬዚዳንት በመግለጫቸው ጋዜጠኞች ለእግር ኳስ ማደግ ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን በማስታወስ በቀጣይም ለእግር ኳስ እድገት ለመገናኛ ብዙኃንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በጋራ የሚሰራ ይሆናል ብለዋል።
ሼር ካምፓኒው የሀገሪቱን እግር ኳስ ለማሳደግ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።
በተጨዋቾች በኩል የአካል ብቃት ችግርና፣ ፍጥነትን ማሻሻል አሁንም ብዙ መሥራት እንደሚገባና ሌሎች ጉድለቶችን መቅረፍ ከተቻለ እግር ኳሱን ከአፍሪካ ሀገራት ቁንጮ ላይ ማድረስ ይቻላል ብለዋል።
የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በዚህ ዓመት ከሌላው ጊዜ በተለየ በዲ ኤስ ቲቪ የቀጥታ ሥርጭት እየተሰጠው አራተኛ ሳምንት ላይ መድረሱ ይታወቃል።