ኮሚሽኑ ለመተከል ተፈናቃዮች ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገ

49

አሶሳ ታህሳስ 22 / 2013 (ኢዜአ) በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ለመተከል ተፈናቃዮች ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገ፡፡

በኮሚሽኑ  የአሶሳ አስተባባሪ ሚስ ቪክቶሪያ ኮፓ  ድጋፉን  ዛሬ በአሶሳ ከተማ  ለክልሉ አደጋ ስጋት እና ስራ አመራር ኮሚሽን አስረክበዋል፡፡

አስተባባሪዋ ድጋፉን ባስረከቡበት ውቅት እንደተናገሩት፤ ኮሚሽኑ የመተከልን ተፈናቃዮች ለመደገፍ ከክልሉ  ጋር በመቀናጀት እየሠራ ነው፡፡

ከድጋፉ  መካከል 13 ሺህ ብርድ ልብሶች እንዲሁም  የአልጋ አጎበሮች፣ ምንጣፎች፣ የተለያዩ የምግብ ማብሰያ ቁሳቁሶች ይገኙበታል፡፡

ይህም ከአራት ሺህ በላይ ቤተሰቦችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ   ሚስ ቪክቶሪያ አስረድተዋል፡፡

ድጋፉን የተረከቡት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አደጋ ስጋት እና ስራ አመራር ኮሚሽነር አቶ ታረቀኝ ተሲሳ በበኩላቸው፤ በመተከል ዞን የተፈናቀሉትን ወገኖቻችንን በመንግስት አቅም ብቻ ለመደገፍ አዳጋች በመሆኑ መንግሥት ኀብረተሰቡን ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት ረጂ ድርጅቶችም እንዲያግዙ ጥሪ መቅረቡን አስታውሰዋል፡፡

ጥሪውን ተቀብሎ ኮሚሽኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሰጠው ምላሽ   ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ድጋፉ በዞኑ  በርካታ ተፈናቃዮች በሚገኙበት ቡለን እና ድባጤ ወረዳዎች በአጭር  ቀናት ውስጥ  እንደሚደርስ አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም