ቀጥታ፡

የጤና ሙያ ማህበራት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያደርጉትን እንቅስቃስ እንዲያጠናክሩ ተጠየቁ

አዲስ አበባ ታህሳስ 22/2013 (ኢዜአ) የጤና ሙያ ማህበራት ኮቪድ-19 ወረርሽኝን በመከላከል የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ እንዲያጠናክሩ የጤና ሚኒስቴር ጠየቀ።

በኮቪድ-19 ምላሽ ፕሮጀክት ወረርሽኙን ለመከላከል አስተዋጽኦ ላደረጉ 11 የጤና ሙያ ማህበራት፣ የጤና ተቋማትና ግለሰቦች በዛሬው እለት እውቅና ተሰጥቷል።

በዚህም የዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል፣ ኤካ ኮተቤ ሆስፒታልና ሚሌኒየም የኮቪድ-19 ህክምና ማዕከል እንዲሁም አርቲስት ሰለሞን ታሼ (ጋጋ) የእውቅና ምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።

በኢትዮጵያ ሚድዋይፎች አስተባባሪነት የተተገበረው ፕሮጀክቱ 11 የጤና ሙያ ማህበራት ተሳታፊ ያደረገና የጤናውን ዘርፍ ባለሙያዎችንና የኀብረተሰቡን የኮቪድ-19 ግንዛቤ ማሳደጊያ መርሃ ግብሮች የተካሄዱበት ነው።  

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አለምፀሀይ ጳውሎስ  የጤና ሙያ ማህበራትና ባለሙያዎች ኮቪድ 19ን ለመዋጋት ላበረከቱት አስተዋፅኦ አመስግነው፣ በቀጣይም ትብብሩ መቀጠል ይገባዋል ብለዋል።

ማህበራቱ በማህበረሰቡ ዘንድ ያለው መዘናጋት ለመቀነስም ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

በሽታው እያሳየ ያለው ባህርይ ለመቀየር በአንድነትና በትብብር መስራት እንደሚጠበቅ በመጠቆም።

የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ዘነበ አካለ እንዳሉት ፕሮጀክቱ ላለፉት ሶስት ወራት ለኮቪድ-19 እንዴት ምላሽ መስጠት ይቻላል በሚል ሲተገበር የቆየና በጤና ሚኒስቴር በጀት የተተገበረ ነው።

በዘርፉ የሚንቀሳቀሱ 11 ጤና ሙያ ማህበራት ለኮቪድ-19 በቅንጅት ምላሽ ለመስጠት ለኀብረተሰቡና ለጤና ባለሙያዎች ያቀረቡት መነሻ ጽሁፍ በሚኒስቴሩ ተቀባይነት አግኝቶ ወደ ተግባር መገባቱን ተናግረዋል ።

በፕሮጀክቱ የኀብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ በተለያዩ ቦታዎች በመዘዋወርና መገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም ትምህርት የተሰጠ ሲሆን፣ የጤና ባለሙያዎች 4 ሺህ 750 መሰልጠናቸውን አስታውቀዋል።

ጥምረቱ በቀጣይም ከጤና ሚኒስቴርና ከክልል ጤና ቢሮዎች ጋር በትብብር ይሰራል ነው ያሉት።

ለፕሮጀክቱ 20 ሚሊዮን ብር በጀት በመመደብ የጤና ባለሙያዎችን  ዕውቀትና ክህሎት ለማሳደግ መሰራቱን የገለፁት ደግሞ በጤና ሚኒስቴር የሰው ሃብት ልማት ዳይሬክተር አቶ አሰግድ ሳሙኤል ናቸው።

ማህበራቱ በፕሮጀክቱ  አፈጻጸም ያሳዩትን ቁርጠኝነትና ተነሳሽነትም አድንቀዋል።

ኮቪድ-19 ባህሪውን ቀይሮ እየመጣ በመሆኑ ከዚህ ጋር ተያይዞ መሰራት ያለባቸው ተግባራት መጠናከር  እንዳለባቸው ያሳያልም ብለዋል።

የጤና ባለሙያዎችን እውቀትና ክህሎት ዘላቂነት ባለው መልኩ በተከታታይ ሙያ ማጎልበቻ ስርዓት ለመገንባት ከሙያ ማህበራትና ከክልል ጤና ቢሮዎች ጋር በትብብር እንደሚሰራ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ለባለሙያዎች በኢንተርኔት (ኦንላይን) ስልጠና ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አቶ አሰግድ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም