ቀጥታ፡

ፍርድ ቤቱ የኢትዮጵያን ወታደራዊ ሚስጥር አሳልፈው ሰጥተዋል በሚል ወንጀል የተጠረጠሩት ብርጋዴል ጀኔራል ኪዱ አለሙ ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቀደ

ታህሳስ 22/2013( ኢዜአ) የፌደራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ወታደራዊ ከፍተኛ መኮንን የነበሩትና የኢትዮጵያን ወታደራዊ ሚስጥር አሳልፈው ሰጥተዋል በሚል ወንጀል በተጠረጠሩት ብርጋዴል ጀኔራል ኪዱ አለሙ ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቀደ፡፡

ተጠርጣሪው በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የጊዜ ቀጠሮ ችሎት የቀረቡ ሲሆን መርማሪ ፖሊስም ያከናወናቸውን የምርመራ ስራዎቹን ለችሎቱ አስረድቷል፡፡

ብርጋዴል ጀኔራል ኪዱ ኬንያ ሆነው ከተለያዩ አካላት ጋር ግንኙነት በመፍጠር የሀገሪቱን ወታደራዊ ሚስጥር አሳልፈው መስጠታቸውን ማስረጃ ሰብስቤያለሁ ብሏል ፖሊስ በማብራሪያው።

ከሕወሃት ፀረ ሰላም ቡድን ተልእኮ በመቀበል በትግራይ ክልል ሰሜን እዝ ላይ ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውንም መረጃ ማሰባሰቡን ነው የገለፀው።

ተጠርጣሪው ኬንያ ሆነው የኦነግ ሸኔ አባላትን በመመልመል ስልጠና ሲሰጡ እንደነበር መርማሪ ፖሊስ ከዚህ በፊት ለችሎቱ ገለጾ አንደነበር የሚታወስ ነው።

በዚህ ዙሪያ የቴክኒክ ማስረጃ ለማሰባሰብ፣ የምስክር ቃል ለመቀበልና ከብሔራዊ መረጃና ደሕንነት ሌሎች ማስረጃዎችን ለማምጣት 14 ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጠይቋል ፖለስ።

"ተጠርጣሪው በበኩላቸው የሚባለውን ወንጀል አልፈፀምኩም፤ በተመደብኩበት ሀገር የዲፕሎማሲ ስራዬን በአግባቡ ሳከናውን የነበረ በመሆኑ የዋስትና መብት አንዲያስከብርልኝ" ሲሉ ጠይቀዋል።

የግራ ቀኝ ክርክሩን ያደመጠው ፍርድ ቤቱ መርማሪ ፖሊስ ከጠየቀው 14 ቀን 11 ቀን በመፍቀድ ለጥር 3 ቀን 2013 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በሌላ በኩል ደግሞ ፍርድ ቤቱ በዚሁ ችሎት የቀረቡ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አመራር የነበሩት ኮማንደር ግርማይ ናይዝጊ መዝገብ የተካተቱ 6 ተጠርጣሪዎች የ10 ሺህ ብር ዋስትና እንዲወጡ ፈቅዷል።

በዚህ መዝገብ የተካተቱት ተጠርጣሪዎች ኮማንደር ግርማይ ናይዝጊ፣ ሌተናል ኮሎኔል ገብረማርያም አርያ፣ ወይዘሮ ተክለብርሃን በርሄ፣ አቶ ዘረሰናይ ገብረዮሀንስ፣ ብርጋዴል ጀነራል ሀየሎም ገብረስላሴ እና አቶ ዳንኤል ገብረመድህን ናቸው።

በዛሬው እለት መርማሪ ፖሊስ ቀሪ የምርመራ ስራዎችን ለማከናወን 14 ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ይፈቀድልኝ ሲል ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

ፍርድ ቤቱም መርማሪ ፖሊስ ዛሬ ያቀረበው የምርመራ ስራ ከዚህ ቀደም በነበረው ችሎት ላይ ካቀረበው የተለየ መረጃ ባለማከተቱ  ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጥያቄውን ውድቅ ማድረጉን አስታውቋል።

በመሆኑም ተጠርጣሪዎቹ እያንዳንዳቸው በ10 ሺህ ብር ዋስ ወጥተው ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው አንዲከታተሉ ፈቅዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም