የኖርዌይ የልማት ትብብር ኤጀንሲ ለአምስት የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች አቅም ግንባታ የሚውል 91 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የኖርዌይ የልማት ትብብር ኤጀንሲ ለአምስት የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች አቅም ግንባታ የሚውል 91 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ
ታህሳስ 22/2013 (ኢዜአ) የኖርዌይ የልማት ትብብር ኤጀንሲ ለአምስት የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች አቅም ግንባታ የሚውል 91 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ።
ኤጀንሲው ድጋፉን ይፋ ያደረገው ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አቅም ግንባታ የሚውል ነው።
የገንዘብ ድጋፉ እንዲገኝ አስተዋፆ ያደረጉት የኢትዮጵያን ኖርዌጃን ፕሮፌሽናል ድርጅት ዋና ዳይሬክተርና 'በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሳውዝ ኖርዌይ' የኮምፒውተር ሳይንስ መምህር ተባባሪ ፕሮፌሰር ሸጋው አናጋው ድጋፉን በሚመለከት ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
ድጋፉ የኖርዌይ የልማት ተራድኦ ድርጅት ለታዳጊ አገራት ያዘጋጀው የ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን የኖርዌይ ገንዘብ ( ክሮነር) የእርዳታ ፕሮግራም ውድድር አካል ነው።
በውድድሩ ከተካፈሉት 199 አመልካቾች መካከል 60 የሚሆኑት ድጋፉን ማግኘታቸውን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያም የዚሁ ድጋፍ አካል መሆኗን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በድጋፉ 20 ሚሊዮን ክሮነር ወይም 91 ሚሊዮን ብር ለማግኘት መቻሏን ነው የተናገሩት።
ከዚሁ ድጋፍ የተገኘው ገንዘብ ለጎንደር፣ጅማ፣ሀዋሳ፣ደብረማርቆስና የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲዎች የአቅም ግንባታ ስራ እንዲውል ድጋፍ ማድረጉንም ተባባሪ ፕሮፌሰር ሸጋው አንጋው የገለጹት።
ድጋፉም በ6 ዓመት ፕሮግራም ተግባራዊ እንደሚሆን ነው የተናገሩት።
ልዩ ፍላጎት፣ሜዲካል ቴክኖሎጂ (ኢ ሄልዝ) እና ከኮምፒውተር ጋር የተገኛኙ የትምህርት ክፍሎች ደግሞ በድጋፉ ትኩረት የሚሰጥባቸው ዘርፎች መሆናቸውንም ገልጸዋል።
በተጨማሪ ድርጅቱ 45 ለሚሆኑ የማስተርስ ተማሪዎች እና 15 የዶክትሬት ተማሪዎች በኖርዌይ የትምህርት እድል እንዲያገኙ የማመቻቸት ስራ እንደሚያከናውንም ተናግረዋል።
በኖርዌይ ያሉ ዩኒቨርስቲዎችና ምሁራን ከኢትዮጵያ አቻቸው ጋር በቅንጅት እንዲሰሩ እንደሚደረግም ነው ያነሱት።
ድጋፉ በስራ እድል ፈጠራ ላይ ያተኮረ ስርዓተ ትምህርት ቀረፃን ያካተተ መሆኑንም ተናግረዋል።
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው ሰላም፣ልማትና እድገት የሚያደርጉትን አወንታዊ አስተዋፆ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም ጥሪ አቅርበዋል።