ቀጥታ፡

ንግድ ባንክ ስራ በመጀመሩ ችግራችን ተቃሏል-የመቀሌ ነዋሪዎች

መቀሌ ታህሳስ 22/2013 (ኢዜአ) -በመቀሌ ተቋርጦ የቆየው የንግድ ባንክ አገልገሎት በመጀመሩ ችግራቸው መቃለሉን ነዋሪዎች ገለጹ።

የባንክ አገልግሎቱ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች እንዲጀምር ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል።

በኢትዮጽያ ንግድ ባንክ መቀሌ ዲስትሪክት በሮማናት ቅርንጫፍ ሲገለገሉ ኢዜአ ካነጋገራቸው ተገልጋዮች  መካከል አቶ ተስፋዬ ኃይሉ  አንዱ ናቸው።

በክልሉ የነበረውን የጸጥታ ችግር ተከትሎ ለወራት የባንከ አገልግሎት ተቋርጦ መቆየቱን አስታውሰዋል ።

"የባንክ አገልግሎቱ ተቋርጦ በመቆየቱ ለችግር ተዳርገን ቆይተናል" ብለዋል

አሁን ላይ የተፈጠረውን ሰላም ተከትሎ በከተማው የንግድ ባንኮች አገልግሎት መሰጠት በመጀመራቸው ችግራቸው መቃለል መጀመሩን አመልክተዋል።

በባንኩ ከቆጠቡት ገንዘብ እስከ 25 ሺህ ብር አውጥተው እንዲጠቀሙ በመፈቀዱ መንግስትን አመስግነዋል።

ለወራት ያህል የባንክ አገልግሎት ተቆርጦ በመቆየቱ ለምግብ መግዣ ገንዘብ በማጣታቸው ለከፍተኛ ችግር ተጋልጠው መቆየታቸውን የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ አበባ አባይ ናቸው።

የባንከ አገልግሎቱ መጀመር  ችግራቸውን እንዳቃለለላቸው በመግለጽ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች  አገልግሎቱ እንዲጀመር ጠይቀዋል።

አቶ በዛብህ አስረስ  በበኩላቸው በከተማው የባንክ አገልግሎት በመጀመሩ ህብረተሰቡ ከገባበት ችግር መላቀቅ መጀመሩን ተናግረዋል።'

አገልግሎቱ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ባለመጀመሩ ህብረተሰቡ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር መጋለጡን ጠቁመዋል።

በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ንግድ ባንኮች ጨምሮ የፋይናንስ ተቋማት ስራ እንዲጀምሩ ጠይቀዋል።

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መቀሌ ዲስትሪክት የሮማናት ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌታቸው መንግሥቱ የባንኩ ሠራተኞች  ለወራት ተቸግሮ የቆየውን ህብረተሰብ ለማርካት የተቀላጠፈ አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም