ለትግራይ ተወላጅ ተፈናቃዮች ማቋቋሚያ ግማሽ ቢሊዮን የሚደርስ ገንዘብ ሊሰባሰብ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ለትግራይ ተወላጅ ተፈናቃዮች ማቋቋሚያ ግማሽ ቢሊዮን የሚደርስ ገንዘብ ሊሰባሰብ ነው
መቀሌ ሀምሌ 14/2010 የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ከተለያዩ የኢትዮጵያ አከባቢዎች በግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ የክልሉ ተወላጆችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚያስችል ዝግጅት ጀምሯል። ተፈናቃዮቹን በዘላቂነት ለማቋቋምም እስከ ግማሽ ቢሊዮን ብር የሚደርስ ገንዘብ ለማሰባሰብ የሚያስችል መርሀ-ግብር እንደሚዘጋጅም ተመልክቷል። የክልሉ መንግስት የተፈናቃዮች ማቋቋሚያ አስተባባሪ ኮሚቴውን ወክለው አቶ ሃይለ አስፋሃ በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት የክልሉ መንግስት ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም አራት ንኡሳን ኮሚቴዎች ተዋቅረው እንቅስቃሴ ጀምሯል። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ በተፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የትግራይ ክልል ተወላጆች መፈናቀላቸውን አስታውሰዋል። በግጭቱ ምክንያት ከኦሮሚያና አማራ ክልሎች ብቻ ከ25ሺ በላይ የትግራይ ክልል ተወላጆች ንብረታቸውን አጥተውና ጉዳት ደርሶባቸው መፈናቀላቸውን ተናግረዋል። “ተፈናቃዮቹ በጊዜያዊነት የሚያገኙት እርዳታ ያለማቋረጥ እንዲሰጣቸው ከማድረግ ባለፈ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ በሚኖሩባቸው አካባቢዎችና ከተሞች ጊዜያዊ መጠለያ እንዲሰራላቸው ይደረጋል” ብለዋል። በክልሉ የገጠር አካባቢዎች የተጠለሉ ተፈናቃዮችም የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ እንደሚሰጣቸው አቶ ሃይለ አስረድተዋል። ከዚሁ በተጨማሪ ነፃ የህክምና አገልግሎት የሚያገኙ ሲሆን ለተማሪዎች ከሚቀጥለው የትምህርት ዘመን ጀምሮ የትምህርት እድል እንዲያገኙ የቁሳቁስና ሌሎች ድጋፎች ከወዲሁ ለማሰባሰብ እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታውቀዋል። ተፈናቃዩቹን በዘላቂነት ለማቋቋምም ከአማራና ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስታትና ከፌዴራል መንግስት ጋር በመሆን እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። የክልሉመንግስት፣የትግራይ መልሶ ማቋቋም/ትእምት/፣ማህበራዊ ረዲኤት ትግራይ/ማረት/፣የግል ባለሃብቶችንና ህዝቡን በማስተባበር የገቢ ማሰባሰቢያ መርሀ-ግብር በቅርቡ ለማስጀመር ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል። በዚህም ተፈናቃዮቹ ሊሰማሩበት የሚፈልጉት የስራ ዘርፍ መለየቱንና ከደደቢት የብድርና ቁጠባ ተቋም ብድር የሚያገኙበት ሁኔታ ተመቻችቶ የአሰራር ሥርዓት መዘርጋቱን አቶ ሃይለ አመልክተዋል።