የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ እስካሁን ከዳያስፖራው ከ7 ሚሊዮን ዶላር በላይ አሰባስቧል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ እስካሁን ከዳያስፖራው ከ7 ሚሊዮን ዶላር በላይ አሰባስቧል
ታህሳስ 22/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ እስካሁን ከዳያስፖራው ከ7 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማሰባሰቡን አስታወቀ።
ለሕይወት አድን የህክምና ቁሳቁሶች የሚውል የእርዳታ ፈንድ ማቋቋሙንም ይፋ አድርጓል።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ላለፉት ሁለት ዓመታት የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝና ከነዚህም ውስጥ በዋንኛነት የሚጠቀሰው ከዳያስፖራው የሚሰበሰብ የገንዘብ እርዳታ መሆኑን ገልጿል።
ከ93 አገራት ከ26 ሺህ በላይ ለጋሾች በማሰባሰብ፣ 48 የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ምዕራፎችን በማቋቋምና በተለያዩ መስኮች የሚያገለግሉ ከ200 በላይ በጎ ፈቃደኞችን በማስተባበር እስካሁን ከ7 ሚሊዮን ዶላር በላይ እርዳታ ማሰባሰቡን ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።
ከዚህም ውስጥ በትረስት ፈንዱ የምዘና መስፈርት መሰረት ለገንዘብ ድጋፍ ብቁ ለሆኑ አምስት የልማት ሥራዎች ፋይናንስ ለማድረግ 1 ሚሊዮን 342 ሺህ ዶላር ሺህ ዶላር ያጸደቀ ሲሆን ፕሮጀክቶቹን ለመጀመር 165 ሺህ 939 ዶላር መለቀቁን አመልክቷል።
በተጨማሪም በሂደት ላይ ለሚገኙ ፕሮጀክቶች አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታዎች እና መመዘኛዎች ሲያሟሉ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚደረግላቸውም አስታውቋል።
በሌላ በኩል በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን አስቸኳይ ፍላጎቶች ግምት ውስጥ በማስገባት የሕክምና ተቋማትን ለማገዝ ለሕይወት አድን የሕክምና ቁሳቁሶች መግዣ የሚውል የ500 ሺህ ዶላር የሕክምና እርዳታ ፈንድ ማቋቋሙንም ነው የገለጸው።
ተጨማሪ 500 ሺህ ዶላር ከለጋሾች በማሰባሰብ የፈንዱን መጠን በአጠቃላይ ወደ 1 ሚሊዮን ዶላር ለማሳደግ የሚያስችል ዘመቻ መጀመሩን ጠቁሟል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመዋጋት ለተላለፈው አገራዊ ጥሪ ምላሽ ከ1 ሚሊዮን 173 ሺህ ዶላር በላይ በመመደብ የጤና ሚኒስቴር ባወጣው መስፈርት አማካኝነት የሕክምና ዕቃዎች ተገዝተው ወደ አገር ቤት መላካቸውን አመልክቷል።
ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ፕሮጀክቶችን እንዲሁም ቅድሚያ የሚሰጣቸውን የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታዎችን መለየት፣ ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል የአሰራር ሂደት እየዘረጋ እንደሆነም አመልክቷል።
ትረስት ፈንዱ እ.አ.አ ጃንዋሪ 1,2021 (ከነገ ጀምሮ) ከሚሰበሰቡ እርዳታዎች ላይ የስራ ማስኬጃ በጀት እንደሚመደብለትና የድርጅቱን የዕለት ከዕለት ስራ የሚከታተል አነስተኛ ጽሕፈት ቤት ለማቋቋም መታቀዱን ገልጿል።
የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ አማካሪ ምክር ቤቱም በተጠናከረ መልኩ በአማካሪነት ተግባሩ መስራቱን እንደሚቀጥልም አስታውቋል።
በገና በዓል ሰሞን በመሰረታዊ የሕክምና እርዳታ እጦት ሕይወታቸው አደጋ ላይ የወደቁ ኢትዮጵያውያንን በማሰብ ዳያስፖራው የተለመደውን ድጋፍ እንዲያደርግ ትረስት ፈንዱ ጥሪውን አቅርቧል።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ከሁለት ዓመት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ (ዶ/ር) በአሜሪካ ካደረጉት ጉብኝት በኋላ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው በቀን ከሚጠጡት ማኪያቶ ላይ ቀንሰው አንድ ዶላር እንዲያዋጡ ያስተላለፉትን ጥሪ ተከትሎ የተመሰረተ ተቋም ነው።
ትረስት ፈንዱ በዋናነት ማህበረሰብ ተኮር ለሆኑ የኢኮኖሚና የማህበራዊ የልማት ፕሮጀክቶች የፋይናንስ ድጋፍ ያደርጋል።