በደቡብ ክልል ፖሊስ የተጣለበትን ህዝብን የመጠበቅ ግዴታውን በአግባቡ እንዲወጣ እንደሚሰራ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ክልል ፖሊስ የተጣለበትን ህዝብን የመጠበቅ ግዴታውን በአግባቡ እንዲወጣ እንደሚሰራ ተገለጸ
ሀዋሳ፣ ታህሳስ 21/2013 (ኢዜአ) ፖሊስ ካለፈው ስህተት ተምሮ የተጣለበትን ህዝብን የመጠበቅ ግዴታውን በአግባቡ እንዲወጣ የሚሰሩ መሆናቸውን የደቡብ ክልል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር አለማየሁ ማሞ ገለጹ።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የ2013 የመጀመሪያው መንፈቅ ዓመት የዕቅድ ክንውን ግምገማና የሥራ ማነቃቂያ መድረክ በኮንሶ ዞን ካራት ከተማ አካሂዷል።
በመድረኩ የክልሉ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነሩ እንዳሉት ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ሳይፈቱ የቆዩ የህዝቦች የመልካም አስተዳደርና የመዋቅር ጥያቄዎች በየደረጃው ሲነሱ ቆይተዋል፡፡
ይህን ተከትሎ ሕጋዊ እና ሕገወጥ እንቅስቃሴዎች ተቀላቅለው ሲቀርቡና በዚህም የተነሳ በክልሉ አንዳንድ አለመግባባቶች ሲፈጠሩ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
የፖሊስ ተልዕኮ ግጭቶችን የማርገብና መቆጣጠር እንደነበር ያስታወሱት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ በዚህ ክልሉን የማረጋጋት ሥራ ውስጥ አዎንታዊ ውጤትና ችግርም ማጋጠሙን አስረድተዋል፡፡
በፀጥታው ዘርፍ ለገጠመው የአሰራር ችግር ሁሉንም መፈረጅ ባይቻልም ከነፈሰው ጋር አብረው የሚሄዱና በሚፈጠሩ አለመግባባቶች ውስጥ ተሳትፎ የነበራቸው አንዳንድ የፖሊስ አባላት ሚናቸው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አሁን ላይ እንደ ሀገር ባለው ሕግን የማስከበር ሂደት ከፌዴራል ፖሊስና በክልሉ ልዩ ኃይል ፖሊስ አጋዥነት መደበኛ ሥራችንን እየሰራን ነው ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ መደበኛው ፖሊስ ካለፈው ስህተት ተምሮ የተጣለበትን ህዝብን የመጠበቅ ግዴታውን በአግባቡ እንዲወጣ የተለያዩ ሥራዎች እንደሚያከናውኑ ተናግረዋል፡፡
በተለይ የህዝብን ደህንነት በአግባቡ ከመጠበቅና ሥጋቶችን አስቀድሞ ከመከላከል አንፃር ለፖሊስ አመራሮች የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ላይ ያተኮረ የማነቃቂያ ሥልጠና መሰጠቱን ጠቁመዋል፡፡
የኮንሶ ዞን ፖሊስ አዛዥ ምክትል ኮማንደር ሠለሞን ከመይታ በበኩላቸው፤ በአካባቢው በቅርቡ በተፈጠሩ የፀጥታ ችግሮች የዜጎች ህልፈትና መፈናቀል መድረሱን አስረድተዋል ፡፡
አሁን ላይ በኮንሶና ኧሌ ህዝቦች መካከል ዕርቅ በማውረድ የተፈጠረውን አለመግባባት ማርገብ መቻሉን ገልጸው ፤ በነበረው ግጭት ውስጥ በተለይ በፖሊስ ኃይሉ ውስጥ አካባቢያዊነትና ለአንድ ወገን ብቻ የመቆም አስተሳሰቦች መስተዋላቸውን ጠቅሰዋል ፡፡
እንደዚህ ዓይነት አስተሳሰብ ከፖሊስ ሥነ ምግባር አንፃር እንደማይጠበቅ አመልክተው፤ ፖሊስ ለሁሉም ዜጎች በማዕከላዊነት ሊቆም ይገባል ብለዋል ፡፡
አክራሪ ብሔርተኝነት ውሎ አድሮ አመራሩንም ወደ እሳት የሚማግድ በመሆኑ የጠራ አስተሳሰብ በመላበስ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም ከሌሎች ዞኑን ከሚያዋስኑ የኀብረተሰብ ክፍሎችና አመራሮች ጋር በመተባበር ዘላቂ ሠላም ለማስፈን ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
የደቡብ ኦሞ ዞን ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ጴጥሮስ ገብሬ በዞኑ የሚገኙ 16 ብሔረሶቦች ጨምሮ አካባቢው ከመላው የኢትዮጵያ ክፍል የመጡ ዜጎችም መኖሪያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሆኖም የፀጥታ ኃይሉ የብሔር ልዩነት ሳይከፋፍለው አንድ በመሆንና ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዞኑ ካለው የብሔረሰቦች ስብጥር የተነሳ ከሀገራዊ ለውጡ ጀምሮ በተደጋጋሚ ለውጡን ለማደናቀፍ በሚሰሩ ኃይሎች ኢላማ እንደሆነ ጠቁመው፤በተለይ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ህግ የማስከበር ሀገራዊ ተልዕኮን በመወጣት ላይ እያለ በከፍተኛ ዝግጅት ዞኑን ለማተራመስ መሞከራቸውን አስረድተዋል ፡፡
በቅርቡ ህዝብን ከህዝብ ጋር ለማጋጨት ታስቦ 290 የሚሆን ገጀራ ወደ ዞኑ ሲገባ በቁጥጥር ሥር መዋሉንም አስታውሰዋል ፡፡
እነዚህ ኃይሎች የህዝቡን ሠላም ለማደፍረስ በተለያየ መንገድ ሲጥሩ ቢቆዩም የፀጥታ መዋቅሩ ከህብረተሰቡና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ባከናወነው ቅንጅታዊ ሥራ በአካባቢው አስተማማኝ ሠላም ማስፈን መቻሉን ገልፀዋል ፡፡
ፈተናዎቹን ያለፍነው ብዙ ብንሆንም እንደ አንዲት ኢትዮጵያ አስበን በመሥራታችን ነው ያሉት ኮማንደር ጴጥሮስ፤ከኀብረተሰቡ ጋር ተናበው መሥራታቸው ለቀጣይም ልምድ እንደሚሆናቸው ገልጸዋል፡፡
በመድረኩ ከሁሉም የክልሉ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች የተወጣጡ የፖሊስ አመራሮች ተሳትፈዋል ፡፡