የመንግስት የልማት ድርጅቶችና የፋይናንስ ተቋማት ዓለም አቀፉን የሂሳብ አያያዝ ስርዓት መተግበር አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
የመንግስት የልማት ድርጅቶችና የፋይናንስ ተቋማት ዓለም አቀፉን የሂሳብ አያያዝ ስርዓት መተግበር አለባቸው
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 21/2013 (ኢዜአ) የመንግስት የልማት ድርጅቶችና የፋይናንስ ተቋማት ዓለም አቀፉን የሂሳብ አያያዝ ስርዓት /አይ.ኤፍ.አር.ኤስ/ መተግበር እንደሚገባቸው የኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ አሳሰበ።
ቦርዱ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብና የሂሳብ አያያዝ ስርዓትን አስመልክቶ ከከፍተኛ ግብር ከፋዮች ጋር ተወያይቷል።
የኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሂክመት አብደላ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የፋይናንስና የሂሳብ አያያዝ ስርዓት በሚፈለገው ደረጃ አልተተገበረም።
የሂሳብ አያያዝ በዓለም አቀፍ ስታንዳርድ መሰረት እንዲሆን መደረጉ የአሰራር ግልጽነት የሚፈጥርና ለውድድርም አመቺ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ስርዓቱ ለግብር አከፋፈል፣ ለብድር አገልግሎት እንዲሁም ለውጭ አገር ባለሃብቶችም ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ ከ70 እስከ 80 በመቶ የሚሆነው ግብር የሚሰበሰበው ከከፍተኛ ግብር ከፋዮች መሆኑን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሯ ስርዓቱን መተግበሩ ግልጽነትና ተጠያቂነትን ከመፍጠር ባሻገር ለኢኮኖሚውም ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።
ስርዓቱን በአገር አቀፍ ደረጃ ለመተግበር ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱንም አክለዋል።
በመሆኑም በአዋጅ በተደነገገው መሰረት እስከ 2015 ዓ.ም ድረስ ሁሉም የመንግስት የልማት ድርጅቶችና የፋይናንስ ተቋማት ዓለም አቀፉን የሂሳብ አያያዝ ስርዓት እንዲተገብሩ ዋና ዳይሬክተሯ አስገንዝበዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ በበኩላቸው ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ስርዓት በዋናነት የንግዱን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
በመሆኑም ተግባራዊነቱን ለመከታተል የተቋቋመው ቦርድ፣ የተለያዩ የመንግስት ተቋማት፣ ባለሃብቶችና ሌሎችም የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም በአዲሱ ፍኖተ ካርታ መሰረት በአገር አቀፍ ደረጃ ሁሉም የመንግስት የልማት ድርጅቶችና የፋይናንስ ተቋማት ላይ ተመሳሳይና ወጥ የአሰራር ስርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል ብለዋል።
አሰራሩ የሁሉም ድርጅቶች ተግባር ከመሆኑ አኳያ ባለሙያዎችን ለማብቃት ስልጠናዎችን ማጠናከርና በስርዓተ ትምህርት ውስጥ በማካተት ወደስራ የሚሰማሩበት ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚገባም አመልክተዋል።