ቀጥታ፡

በመስኖ እየለማ ያለው የስንዴ ምርት ከውጭ የሚገባውን 50 በመቶ ያስቀራል

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 21 /2013 (ኢዜአ) በተያዘው ዓመት በመስኖ እየለማ ያለው የስንዴ ምርት ከውጭ አገር የሚገባውን 50 በመቶ ያህል እንደሚያስቀር የግብርና ሚኒስቴር ገለፀ።

የግብርና ሚኒስትር ዑመር ሁሴን ዛሬ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጋር ባደረጉት ውይይት እንደገለጹት፤ በዚህ ዓመት ከውጭ የሚገባውን 50 በመቶ የስንዴ ምርት ለማስቀረት እየተሰራ ነው።

በዓመት 17 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ከውጭ የሚገባ ሲሆን በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ይህንን በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በመስኖ እርሻ በሁለት ዙር የሚመረተው ስንዴ 300 ሺህ ሄክታር መሬት የሚሸፍን ሲሆን 10 ሚሊዮን ኩንታል የሚደርስ ምርት ለማግኘት እንደሚያስችልም ገልጸዋል።

ከፍተኛ የማምረት አቅም እንዳለ የገለጹት አቶ ዑመር፤ በአፋር ክልል የአዋሽ ወንዝ ያደረሰው የጎርፍ ጉዳት ፈተና ሆኖ እንደነበር አስታውሰዋል።

በአሁኑ የምርት ዘመን ከ90 ሺህ ሔክታር በላይ መሬት በስንዴ የተሸፈነ ሲሆን የምርጥ ዘር፣ የኬሚካልና የአፈር ማዳበሪያ መቅረቡን ተናግረዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ፤ ከሶስት እስከ አምስት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ከውጭ የሚገባውን ስንዴ ሙሉ ለሙሉ በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።

በዓመት ሁለት ጊዜ እየተካሄዱ ያሉት የመስኖ እርሻዎች ለስንዴ ምርት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ ከማዳን ባለፈ በአርሶና አርብቶ አደሩ ዘንድ ከፍተኛ መነሳሳትን መፍጠራቸውን ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል በአሁኑ ወቅት በሱማሌ፣ በደቡብና በኦሮሚያ ክልሎች 18 ዞኖች የአንበጣ መንጋ በመታየቱ የመከላከል ስራ እየተካሔደ መሆኑን አቶ ዑመር ተናግረዋል።

የመከላከሉ ስራ በ13 አውሮፕላኖች በተሽከርካሪና በሰው ኃይል ጭምር አንበጣውን የማሰስና የኬሚካል ርጭት እየተካሔደ መሆኑን ነው የገለጹት።

የአንበጣ መንጋው የነፋስ አቅጣጫና አረንጓዴ ተክልን የሚከተል በመሆኑ ሰብል ወደተነሳባቸው ሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች የመስፋፋት ዕድል እንደሌለው ጠቁመዋል።

ይሁንና አንበጣው በሶማሊያ፣ በኬንያና በደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች የመስፋፋት ሁኔታ እየታየበት መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም