ቀጥታ፡

የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የመረጃዎችን ጥራትና ደረጃ ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 21/2013 (ኢዜአ) የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የመረጃዎችን ጥራትና ደረጃ ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ገለጸ።

የህዝብና ቤት ቆጠራን በተመለከተም በተቋሙ በኩል አስፈላጊ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን ኤጀንሲው ገልጿል።

ኤጀንሲው ያለፉት አምስት ዓመታት የዕቅድ አፈጻፀሙንና በቀጣይ አምስት ዓመታት ለማከናወን በያዛቸው እቅዶቹ ዙሪያ ዛሬ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል።

በቀጣይ እቅዱ ኢትዮጵያ ለመተግበር የገባቻቸውን ዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ ስምምነቶችን አካቷል።

የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢራቱ ይገዙ እንደገለጹት ኤጀንሲው የመረጃዎችን ጥራትና ደረጃ ለማሳደግ የተለያዩ ሥራዎችን እየሰራ ይገኛል።

ከመስክ ተአማኒነት ያላቸውን መረጃዎች ፈጣን በሆነ መንገድ ለመሰብሰብ ቴክኖሎጂን ከመጠቀም ባለፈ የሠራተኞችን አቅም ለማሳደግ እንደሚሰራም ገልጸዋል።

እቅዱ በዋናነት ተፈላጊውን የጥራት መስፈርቶች ያሟላ፣ ወቅታዊ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው መረጃ ለመስጠት ያስችላል ብለዋል።

ባለፉት አምስት ዓመታት የዕቅድ አፈጻጸም ኤጀንሲው መረጃን በመተንተን እና ተደራሽ በማድረግ በኩል የተሻለ አፈጻጸም እንደነበረው አቶ ቢራቱ አስታውሰዋል።

መረጃዎችን ከመሰብሰብ ባለፈ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ እንዲሁም የመረጃዎችን ስፋት ማሳደግ መቻሉንም በጥንካሬ አንስተዋል።

በአንጻሩ የስታትስቲክስ ሕግ ለማዘጋጀት የተያዘው ዕቅድ አለመፈጸሙ እንዲሁም የሕዝብ እና ቤቶች ቆጠራ በታሰበው ጊዜ አለመካሄዱ ውስንነቶች መሆናቸውን ነው የተናገሩት።

የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ አበራሽ ታሪኩ በበኩላቸው ዕቅዱ የአሥር ዓመቱን መሪ እቅድ መሰረት አድርጎ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

የህዝብና ቤት ቆጠራን በተመለከተ አገራዊና ህገ መንግስታዊ ሥራ በመሆኑ እንደ አስፈጻሚ ተቋም ከመንግስት የሚሰጥ አቅጣጫ በመጠበቅ ላይ ቢሆኑም በተቋሙ በኩል ተገቢ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ቆጠራ ባይካሄድም ከዚህ ቀደም በተደረገው የህዝብና ቤት ቆጠራ የተገኙ አመላካቾች ለተለያዩ ጥናቶች ጥቅም ላይ እየዋሉ መሆኑንም ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።

"የመረጃዎችን ጥራትና ደረጃ ለማሳደግ እየተሰሩ ባሉ ሥራዎች ከዚህ በፊት በወረቀት ሲሰበሰቡ የነበሩ መረጃዎችን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ከመስክ በቀጥታ ወደ መረጃ ክፍል በጥራት እና በፍጥነት እንዲደርሱ እየተደረገ ነው" ብለዋል።

በቀጣይም አዳዲስ የመጡ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀምና የሠራተኞችን አቅም በመገንባት የተሻለና ተአማኒ መረጃ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም