የሕዝቦችን አንድነት በሚያጎለብቱ ስራዎች ብዙዎችን የምትመስል ኢትዮጵያን መፍጠር ይቻላል - የታሪክ ምሑራን - ኢዜአ አማርኛ
የሕዝቦችን አንድነት በሚያጎለብቱ ስራዎች ብዙዎችን የምትመስል ኢትዮጵያን መፍጠር ይቻላል - የታሪክ ምሑራን
ታህሳስ 21/2013 (ኢዜአ) ሕዝቦችን አንድ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ የበለጠ በመስራትና ልዩነቶችን በማክበር ብዙዎችን የምትመስል ኢትዮጵያን መፍጠር ይቻላል ሲሉ የታሪክ ምሁራን ተናገሩ።
የታሪክ ምሁራን ወጣቱ ትውልድ የአገሩን ታሪክ በትክክል እንዲረዳ ኃላፊነታቸውን መወጣት እዳለባቸውም ተገልጿል።
ኢትዮጵያዊያን የመቻቻልና የአብሮነት እሴቶች እንዲሁም የጋራ የተጋድሎ ታሪክ ያላቸው ሕዝቦች እንደሆኑ የታሪክ መዛግብት ያነሳሉ ።
በዘመናት አብሮ የመኖር ታሪካቸው የባሕልና ወግ ትስስር የገነቡም ናቸው፤ ይሁንና አሁን አሁን በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉት ድርጊቶች የቀደመውን ታሪክ የሚሸረሽሩ ናቸው።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የቅርስ ጥናት ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፈሰር ዶክተር አየለ በከሪ 'ኢትዮጵያዊያን የዳበረና ዘርፈ ብዙ ታሪክ ያለን ሕዝቦች ነን' ይላሉ።
ኢትዮጵያዊያን በንግድ፣ በባህልና በማኀበራዊ መስተጋብሮች የነበራቸው ግንኙነት በዋነኝነት የሚገለፅ መሆኑን ተናግረዋል።
አሁን በአገሪቷ እዚህም እዚያም የሚታዩ ግጭቶችና መፈናቀሎች በሕዝቦች አብሮ የመኖር ታሪክ እንዳልነበሩ የታሪክ ምሁሩ ገልፀዋል።
በቀደመው የኢትዮጵያ ታሪክ በአስተዳደር የስልጣን እርከን ከሚነሱ አለመግባባቶች በቀር ሕዝቦች እርስ በእርስ የተጋጩበት ታሪክ እንዳልነበረ ዶክተር አየለ ተናግረዋል።
ይህን መልካም የአብሮነት ታሪክ ትውልዱ እንዲያውቀው በመፅሐፍ፣ በፊልም፣ በድራማና በተለያዩ መንገዶች በተከታታይና ያለመሰልቸት በማቅረብ የሕዝቦችን ጠንካራ ግንኙነት መፍጠር ይቻላል ብለዋል።
የታሪክ ምሁራንም ወጣቱ ትውልድ የአገሩን ታሪክ በትክክል እንዲረዳ የበኩላቸውን መወጣት ቢችሉ ይህን መፍጠር ይቻላል ሲሉ እምነታቸውን ገልፀዋል።
በአርሲ ዩኒቨርስቲ የታሪክ መምህር ዶክተር አለምሰገድ ደበሌ ኢትዮጵያዊያን ከሚያጋሯቸው በርካታ እሴቶች አንዱ የሆነውን 'ታሪክ'ን በአግባቡ መረዳት አስፈላጊ ነው ይላሉ።
ኢትዮጵያዊያን በሃይማኖት፣ በባሕልና በቋንቋ ቢለያዩም በጋብቻ፣ በንግድ ግንኙነትና በሌሎችም ማኅበራዊ ግንኙነቶች ተሳስረው የኖሩ ሕዝቦች እንደሆኑም ተናግረዋል።
ዶክተር አለምሰገድ በአገሪቷ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች የቀደመውን የአብሮንት ታሪክ በአግባቡ ካለመረዳት እንደሚመነጩም ጠቁመዋል።
ወጣቱ ትውልድ የአገሩን ታሪክ በተገቢው መንገድ እንዲያውቅ በማድረግ እየተከሰቱ ያሉትን ችግሮች ማስወገድ ይቻላል ብለዋል።
ሕዝቦችን አነድ የሚያደርጉት ላይ የበለጠ በመስራት፣ በመቻቻልና ልዩነቶችን በማክበርም ብዘዎችን የምትመስል ኢትዮጵያን መፍጠር ይቻላል ሲሉም ተናግረዋል።