በጤናው ዘርፍ የተመዘገቡ ውጤቶችን ለማስቀጠል በመስኩ ቁጥጥር የሚያደርጉ አካላት ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባ ተጠቆመ

12
ድሬዳዋ ሀምሌ14/2010 በጤናው ዘርፍ የሚስተዋሉ የተለያዩ ችግሮችን በመፍታት በዘርፉ የተመዘገቡ ውጤቶችን ለማስቀጠል በመስኩ ቁጥጥር የሚያደርጉ አካላት ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ።   የጤና ዘርፉ ተቆጣጣሪ አካላት ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም ግምገማ በድሬዳዋ እየተካያሄደ ነው፡፡ በመድረኩ ላይ የተገኙት የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሠሀራላ  አብዱላሂ እንደተናገሩት ባለፉት ዓመታት በጤና ዘርፍ በተሰሩ ሥራዎች የእናቶችና ህጻናት ሞት ቀንሷል፤ ተላላፊ በሽታዎችን በመቆጣጠር በኩልም አበረታች ለውጦች ተመዝግበዋል፡፡ እነዚህን ውጤቶች ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ህዝቡን ለምሬት እየዳረጉ የሚገኙትን ህገ-ወጥ የምግብና የመድኃኒት ንግድ መስፋፋት፣ የጤና ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር፣ የጤና ባለሙያዎች የሥነ-ምግባር ጉድለቶችን ማስቀረት ይገባል። ለእዚህም በጤና ዘርፍ ቁጥጥር የሚያደርጉ አካላት ጠንካራ ቅንጅት በመፍጠር መስራት እንዳለባቸው ነው ሚኒስትር ዴኤታዋ የገለጹት፡፡ " በየደረጃው ያሉ የዘርፉ ተቆጣጣሪ አካላት ተቀናጅተውና ተደራጅተው መስራታቸው በጤናው መስክ ለሰው ሕመምና ሞት ምክንያት የሆኑትን ህገ-ወጥ  ተግባራት ለማስቆም ያስችላል" ብለዋል፡፡ " ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ እንደሌላው የሥራ ዘርፍ ለቁጥጥር ሥራው ተገቢ ድጋፍ  ሲያደርግ እንዳልነበር አስታውሰው በአዲሱ በጀት ዓመት የቁጥጥር ሥራ እንዲጠናከር ድጋፍ እንደሚያደርግ አመልክተዋል፡፡ የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒት፣ የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን  ዋና ዳይሬክተር አቶ የሁሉ ደነቀው በበኩላቸው እንዳሉት ህብረተሰቡ  ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ በየደረጃው የተቋቋሙ የምግብ፣ የመድኃኒት፣ የጤና አገልግሎት ተቆጣጣሪ አካላት የማይተካ ሚና አላቸው። "ተቆጣጣሪ አካላት ባከናወኗቸው ተግባራት ለውጥ ቢኖርም ውጤቱ ከክልል ክልል፣ ከአካባቢ አካባቢ እንደሚለያይና በቀጣይ  ተመሳሳይ ውጤት እንዲመዘገብ በትኩረት ይሰራል" ብለዋል። የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ጥበቃ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሙሉቀን አርጋው በበኩላቸው  በተለያዩ አካባቢዎች መጠኑና ደረጃ ቢለይም ለህብረተሰቡ ጥራቱና ደረጃውን ያልጠበቁ ምግቦች እየቀረቡ መሆኑን ገልጸዋል። ሕብረተሰቡ ከጤና ስርዓት ውጪ በማይገቡ መድኃኒቶችና የህክምና ግብአቶች ተጎጂ ከመሆን ባለፈ የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት ማረጋገጫ   በሌላቸው አንዳንድ የጤና ተቋማትና ባለሙያዎች ለጉዳት እየተዳረገ መሆኑንም አመልክተዋል። " በመሆኑም የዘርፉ ተቆጣጣሪዎች እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ህዝቡን ያሳተፈ የቁጥጥር ሥራ ማጠናከርና ተገቢውን አስተማሪ እርምጃ መውሰድ አለባቸው" ብለዋል። የድሬዳዋ ጤና ጥበቃ ቢሮ ከዘርፉ ተቆጣጣሪዎች ጋር ይበልጥ ተቀራርቦና ተቀናጅቶ ለመስራት ኃላፊነቱን እንደሚወጣም አረጋግጠዋል፡፡ ለሦስት ቀናት በሚቆየው የግምገማ መድረክ ላይ የፌደራል የምግብ፣ የመድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለሥልጣን፣ የየክልሉ የጤናና ጤና ነክ አገልግሎቶችና ግብአቶች ጥራት ተቆጣጣሪ አካላት፣ የጤና ተቋማት፣ የምግብና መጠጥ አምራች ተቋማትና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በመሳተፍ ላይ ናቸው።                
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም