በባሌ ሮቤ ግለሰቦች ቤት ተከማችተው የነበሩ 410 ቦንዳ የልባሽ ጨርቅ እና ጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ - ኢዜአ አማርኛ
በባሌ ሮቤ ግለሰቦች ቤት ተከማችተው የነበሩ 410 ቦንዳ የልባሽ ጨርቅ እና ጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ
ጎባ ታህሳስ 21/2013 (ኢዜአ) በባሌ ዞን ሮቤ ከተማ በግለሰቦች ቤት በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ 410 ቦንዳ የልባሽ ጨርቅ እና የጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ፖሊስ አስታወቀ።
በኮንትሮባንድ ሀገር ውስጥ የገባው ልባሽ ጨርቁ ከሶስት ሚሊዮን 400ሺህ ብር በላይ እንደሚገመት ተመልክቷል።
የከተማዋ ፖሊስ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ኮማንደር ዳዊት ገንዶ እንደገለጹት የልባሽ ጨርቅ ቦንዳዎች እና ጦር መሳሪያዎቹ የተገኙት በህብረተሰቡ ጥቆማ መሰረት የጸጥታ አካላት ታህሳስ 15 ቀን 2013 ዓ.ም ባደረጉት ድንገተኛ ፍተሻ ነው።
የጦር መሳሪያዎቹ ስምንት ሽጉጦች እና አንድ ክላሽንኮቭ ጠብመንጃ መሆናቸውን ጠቅሰው ልባሽ ጨርቁ ጨምሮ በቤታቸው የተገኘባቸው አራት ግለሰቦች በተጠርጣሪነት መያዛቸውንና ጉዳያቸው ተጣርቶ ለፍርድ ቤት እንደሚቀርብ አስረድተዋል።
ህገ ወጥነትን ለመከላከል ህብረተሰቡ እያደረገ ያለውን ትብብር ያደነቁት ኮማንደሩ፤ ወንጀልን ለመግታት ወደፊትም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ መልዕክታቸውን አሰተላልፈዋል።