በተቋማት የሚታየው የአሰራር ክፍተት ገንዘብ በቀላሉ ወደ ውጭ ሀገር እንዲሸሽ ዕድል ፈጥሯል- የፋይናንስ ደህንነት መረጃ ማእከል - ኢዜአ አማርኛ
በተቋማት የሚታየው የአሰራር ክፍተት ገንዘብ በቀላሉ ወደ ውጭ ሀገር እንዲሸሽ ዕድል ፈጥሯል- የፋይናንስ ደህንነት መረጃ ማእከል
አዲስ አበባ ታህሳስ 21/2013 (ኢዜአ) በባንኮችና በተለያዩ የመንግስት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት የሚታየው የአሰራር ክፍተት ገንዘብ በህገ ወጥ መንገድ በቀላሉ ከሀገር እንዲሸሽ እያደረገ መሆኑን የፋይናንስ ደህንነት መረጃ ማዕከል አስታወቀ።
ኢትዮጵያ ከ146 የዓለም አገሮች ጋር በመተባበር በህገ ወጥ መንገድ ከአገር የሸሸውን ገንዘብ የማስመለስ ስራ ተጀምራለች።
በፋይናንስ ደህንነት መረጃ ማዕከል የክትትልና ቁጥጥር ቡድን መሪ እንዲሁም የፋይናንስ ወንጀሎች ከፍተኛ የፍተሻ ተንታኝ ገንዘብ ከአገር የሚሸሽባቸውን የተለያዩ መንገዶችን አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ ገንዘብ በህገ ወጥ መንገድ ወደ ውጭ ከሚሸሽባቸው ምክንያቶች አንዱ በባንኮችና በተለያዩ የመንግስት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት የሚታየው የአሰራር ክፍተት መሆኑን ባለሙያዎቹ ይገልፃሉ።
ከባንክ ደብተር አወጣጥ ጀምሮ ህገ ወጥ ድርጊቶችን ለሚፈጽሙ ግለሰቦችና ድርጅቶች የሙያ እገዛ ማድረግ በተቋማቱ ላይ ከሚታዩ ክፍተቶች መካከል መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።
በፋይናንስ ደህንነት መረጃ ማዕከል የፋይናንስ ወንጀሎች ከፍተኛ የፍተሻ ተንታኝ አቶ ዮናስ ማሞ እንደሚሉት በኢትዮጵያ ገንዘብ የማሸሽ ወንጀል በተለያዩ ምከንያቶች ይፈፀማል።
በተለያዩ ህገ-ወጥ መንገዶች የተገኘን ገንዘብ በዘመድ አዝማድ ስም ወደ ተለያዩ አገሮች ማዘዋወር አንዱና ዋነኛው ምክንያት መሆኑን አብራርተዋል።
እንደ አቶ ዮናስ ገለጻ በኢትዮጵያ በብዛት የሚከናወኑ ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውሮች የሚፈፀሙት ሀሰተኛ መታወቂያን በመጠቀም ነው።
በዚህ ረገድ በባንኮችና ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ላይ የሚታየው የአሰራር ክፍተትና ቸልተኝነት የራሱን ድርሻ አለው ብለዋል።
ከባንኮች የአሰራር ክፍተትና ቸልተኝነት ባለፈ በኢንቨስትመንት ስም ወደ አገር የሚገቡ አንዳንድ ህገ ወጥ ግለሰቦች ለድርጊቱ መባባስ ምክንያት መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በዚህ ሂደት በኢንቨስትመንት ስም ለማሽነሪዎች የተጋነነ ዋጋ በማቅረብ ገንዘቡ ወደ ውጭ አገር እንዲሸሽ የሚደረግበት አይነተኛ የወንጀል መፈፀሚያ ዘዴ መሆኑንም አቶ ዮናስ አስረድተዋል።
በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክና የገቢዎች ሚኒስቴር በቀጣይ በህገ ወጥ መንገድ በውጭ አገሮች የሚቀር ገንዘብን ትኩረት አድርገው በመቆጣጠር ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያ 164 አገሮች የሚገኙበት የፋይናንስ ደህንነት መረጃ ማዕከል አባል ከሆነች አንድ ዓመት ሊሞላት ነው።
አገሮቹ በፋይናንስ ደህንነት ጉዳይ እርስ በእርስ መረጃ ይቀያየራሉ፤ በህገ ወጥ መንገድ የሸሸ ገንዘብ እንዲመለስ የሚያስችሉ ስራዎችንም በጋራ በማከናወን ላይ መሆናቸው ተገልጿል።
በስምምነቱ መሰረት በህገ ወጥ መንገድ ያገኙትን ገንዘብ ያሸሸ ማንኛው ግለሰብ ወይም ድርጅት የት አገር እንዳለና በምን ስራ ላይ እንደተሳተፈ ከዚያ ባለፈ አሁን ያለበትን ሁኔታ መረጃ ማግኘት ይቻላል ብለዋል አቶ ዮናስ።
የኢትዮጵያን ሰላምና መረጋጋት የማይፈልጉ የውስጥና የውጭ ሃይሎች የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉት ከአለም አቀፍ ገንዘብ አስተላላፊዎች ዕውቅና ውጭ መሆኑ ተገልጿል።
በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶችና የሽብር ተግባራት በህገወጥ መንገድ የተገኘና የተዘዋወረ ገንዘብ የሚደገፉ በመሆናቸው ድርጊቱን ከምንጩ ማድረቅ ካልተቻለ ችግሩን ማስቆም አዳጋች ይሆናል።
የአፍሪካ አገሮች በየዓመቱ 88 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ሀብታቸው በሕገ ወጥ መንገድ ከአፍሪካ ውጭ ወዳሉ የተለያዩ አገሮች እንደሚሸሽ የመንግሥታቱ ድርጅት ያደረገው ጥናት ያመለክታል።
በኢትዮጵያም ኢህአዴግ ወደ ሥልጣን መጥቶ በቆየባቸው ዓመታት 30 ቢሊዮን ዶላር በሕገ ወጥ መንገድ መሸሹን መረጃዎች ያመለክታሉ።