አስፈጸሚውን በመቆጣጠር የመተከል የጸጥታ ችግር ለመፍታት እንደሚሰሩ የምክር ቤት አባላት ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
አስፈጸሚውን በመቆጣጠር የመተከል የጸጥታ ችግር ለመፍታት እንደሚሰሩ የምክር ቤት አባላት ገለጹ
አሶሳ ታህሳስ 21/2023 (ኢዜአ) አስፈጻሚውን አካል በመቆጣጠር የመተከልን ዞን የጸጥታ ችግር ለመፍታት በተቀናጀ አግባብ እንደሚሰሩ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አባላት ገለጹ፡፡
የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ አቶ ታደለ ተረፈ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የመተከል ዞን የጸጥታ ችግር የበርካታ ንጹሃንን ሕይወት ቀጥፏል፣ አካል አጉዱሏል፤ መፈናቀል አስከትሏል፡፡
ድርጊቱም አሳዛኝ እና አንገት አስደፊ ነው ብለዋል፡፡
በመተከል ዞን የሚኖረው ኀብረተሰብ ፍላጎት በሠላም ወትቶ መግባት እንደሆነ የተናገሩት አፈ-ጉባኤው፤ የዜጎች ደህንነት በማስቀደም የመሠረተ ልማት እና መልካም አስተዳደር እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ ምክር ቤቱ በህግ የተሰጠውን አስፈጻሚውን አካል የመቆጣጠር ሃላፊነቱን በሚገባ ለመወጣት እና የህብረሰተቡን ሠላም ለመመለስ የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች በተቀናጀ አግባብ እንዲሠሩ እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡
ሌላው የምክር ቤቱ አባል ወይዘሮ ሻዕቢያ መሃመድ በበኩላቸው የመተከል ጥቃት በክልሉ ያልተለመደ ክስተት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በብዙ ውጣውረድ ተሰቃይቶ የሚኖረው የዞኑ ህዝብ ውድ ሕይወቱን ሊያጣ አይገባም ፤ የዞኑ ነዋሪዎች በቆዳ ቀለም ቢለያዩም ኢትዮጵያዊ ናቸው ብለዋል፡፡
የመተከል የጸጥታ ችግር የፖለቲካ ሴራ እንዳለበት አመልክተው፤ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ህዝብን የማጋጨት ድርጊት ማስቆም አለብን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
እየሞተ የሚገኘውን የወከለንን ህዝብ ወርደን የማዳን ሥራ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
በመተከል ንጹሃን ዜጎች ላይ የተፈጸመው ጭፍጨፋ የማይገባ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ አቶ ኢታና ቁጃ ናቸው፡፡
በመተከል ግጭት ልዩ ፍላጎት ያላቸው ህገ-ወጥ ቡድኖች እና ግለሰበች እንዳሉ አመልክተው፤ ይህም የነዋሪዎችን አንድነት ሸርሽሯል ብለዋል፡፡
በመተከል ህይወታቸውን ያጡት የሃገራችን ዜጎች ናቸው ያሉት አቶ ኢታና፤ እንደህዝብ ተወካይ ለማንም ባለመወገን ችግሩን ለመፍታት በቅንነት እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በካማሽ የተከሰተውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት የተወሰደውን እርምጃ እንደ ተሞክሮ ወስደን ተግባራዊ እናደርጋለን ሲሉ አስታውቀዋል፡፡
ሌላው የምክር ቤቱ አቶ ሳላህ ረሃማቶላ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህዝብ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በቅርበት የመጠበቅ አደራ ከኢትዮያውያን ተሰጥቶታል ሲሉ ተናገረዋል፡፡
የመተከል ግጭት ደግሞ ገድቡን የማደናቀፍ ዓላማ እንዳለው አመልክተው ፤ በዞኑ የህግ የበላይነትን የማስፈን ስራ እንዲሳካ በግጭቱ የተሳተፉ ሁሉ ለፍርድ እንዲቀርቡ የሚሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡