በጋምቤላ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመግታት የህብረተሰቡ ተሳትፎ እንዲጠናከር ተጠየቀ

116
ጋምቤላ ሀምሌ 14/2010 በጋምቤላ ክልል እየተካሄደ ያለውን ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ለመግታት በሚደረገው ጥረት የህብረተሰቡ ተሳትፎ ሊጠናከር እንደሚገባ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ። ኮሚሽኑ ሰሞኑን በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ባደረገው የተጠናከረ ክትትል 10 የእጅ ቦምቦችንና 69 ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገልጿል። የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ቡን ውዊ ለኢዜአ እንዳሉት ክልሉ ከደቡብ ሱዳን ጋር ካለው ሰፊ የድንበር ወስን ጋር ተያይዞ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ወደ ክልሉ እየገባ ነው። ኮሚሽኑ ካለፈው ሰኔ ወር አጋማሽ ጀምሮ ባደረገው ክትትል አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ብቻ በክልሉ የተለያዩ ወረዳዎች 66 የክላሽን ኮፕ እና ሦስት የብሬን መትረየስ ጠመጃዎችንና 10 የእጅ ቦምቦችን ከሰባት ህገ- ወጥ የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪና ደላላ ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገልጸዋል። የመጡት የጦር መሳሪዎቹ የተያዙት ከደቡብ ሱዳን በጋምቤላ በኩል አድረጋው ወደ መህል አገር በተለይም ወደ ደምቢዶሎ ለመውስድ ሲሞከር መሆኑን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል። እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ የጦር መሳሪያዎችና ተጠርጣሪ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ሊውሉ የቻሉት በህብረተሰቡ ጥቆማና ፖለስ  ባደረገው የተጠናከር የክትትልና የቀጥጥር ሥራ ነው። ኮሚሽኑ በአሁኑ ወቅት በተጠርጣሪዎች ላይ መረጃ የማጣራት ሂደት እያከናወነ መሆኑንና ሂደቱ እንደተጠናቀቀም ጉዳያቸው ለፍርድ ቤት እንደሚቀርብ ተናግረዋል። "ኮሚሽኑ ህግ ወጥ የጦር መሳሪዎች በአገር ማህበራዊና ኢኮኖሚዊ እንቅስቃሴዎች ላይ የሚያደረሰውን ጉዳት በመገንዘቡ በአሁኑ ወቅት ህዝባዊ ንቅናቄ በመፍጠር በተቀናጀ መንገድ እየሰራ ነው" ብለዋል። በመሆኑም ህገ - ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውሩን ለመግታት በሚደረገው ጥረት የህብረተሰቡ ተሳትፎና ትብብር መጠናከር እንዳለበት ኮሚሽነር ቡን ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም