ረቂቅ ሕጉ የወንጀል ተጠርጣሪን የፍርድ ሂደት ከሠብዓዊ መብት መርሆዎች አንፃር ማየት አለበት - ኢዜአ አማርኛ
ረቂቅ ሕጉ የወንጀል ተጠርጣሪን የፍርድ ሂደት ከሠብዓዊ መብት መርሆዎች አንፃር ማየት አለበት

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 21/2013 (ኢዜአ) ረቂቅ የወንጀል ሕግ ስነ-ስርዓትና የማስረጃ ሕግ በወንጀል የተጠረጠረን ግለሰብ የፍርድ ሂደት ከዓለም አቀፍ የሠብዓዊ መብት መርሆዎች አንጻር እንዲያይ የኢትዮጵያ ሠብዓዊ መብት ኮሚሽን ምክረ ሃሳብ አቀረበ።
ኮሚሽኑ በረቂቅ የወንጀል ሕግ ስነ-ስርዓትና የማስረጃ ሕግ ከሠብዓዊ መብቶች አንጻር በተሰጡ አስተያየቶች ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መክሯል።
ኮሚሽኑ ረቂቅ ሕጉ ከዓለም አቀፍ የሠብዓዊ መብት መርሆዎች ጋር የሚጣጣም መሆኑን በመፈተሽ ሊሻሻሉ፣ ሊካተቱና ሊቀነሱ ይገባል ያላቸውን ምክረ ሃሳቦች ለውይይት መነሻ አቅርቧል።
ተጠርጣሪዎችን የመያዝ፣ መታሰርና ኃይል አጠቃቀም፣ ፍትሃዊ የፍርድ ስርዓት፣ የወንጀል ምርመራ ዘዴዎችና ለሠብዓዊ መብት ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች ላይ ማሻሻያ እንዲደረግባቸው ለኮሚሽኑ ምክረ ሃሳብ አቅርቧል።
በዳኝነት ስርዓት ውስጥ የክስ አቀራረብ፣ ማስረጃ አሰባሰብና ከፍርድ በኋላ የቅጣት አፈጻጸምን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች ሕጉ ከመጽደቁ በፊት ከሠብዓዊ መብት አንጻር እንዲታዩም ተጠይቋል።
በመድረኩ የተገኙ የጉዳዩ ባለቤቶችም የተዘጋጀው ረቂቅ ሕጉ ከሠብዓዊ መብት አንጻር መታየት ይገባቸዋል ያሏቸውን ሃሳቦች አንስተዋል።
ለተጠርጣሪዎች ሠብዓዊ መብት ትኩረት መስጠት፣ የተፋጠነ ፍትህ የማግኘትና የዋስትና መብት፣ የምስክር አቀራረብና ሌሎችም በረቂቅ እንዲታዩ ከተነሱ ጉዳዮች መካከል ናቸው።
የኢትዮጵያ ሠብዓዊ መብት ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ በረቂቅ ሕጉ የሚሻሻሉ ሃሳቦች ተካተው ጸድቆ ስራ ላይ ሲውል ለፍትህ አስተዳደር መሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
ረቂቅ ሕጉ በኢትዮጵያ የወንጀል ፍትህ አስተዳደር ውስጥ ያልነበሩ አዳዲስ ጽንሰ ሃሳቦችን ማስተዋወቁን በጠንካራ ጎን አንስተዋል።
በተለይ የማስረጃ ሕጉ በኢትዮጵያ የወንጀል ፍትህ ስርዓት ውሰጥ ቀደም ሲል ያልነበረ አዲስ ሕግ መሆኑን ጠቅሰው፤ የወንጀል ስነ-ስርዓት ሕጉ ነባሩን እንደሚያሻሽለው ተናግረዋል።
ኮሚሽነሩ በዓለም አቀፍ የሠብዓዊ መብት ሕግ የተከሳሾችን መብት ከመጠበቅ፣ ማስረጃ ከማሰባሰብና ሌሎች ሊሟሉ የሚገባቸውን ደረጃዎች በማስተዋወቅ በረቂቅ ሕጉ መካተታቸውን በአዎንታዊ መልኩ አቅርበዋል።
ይሁን እንጂ በወንጀል የተጠረጠረ ሰው በቁጥጥር ስር የሚውልበትና ወደ ፍርድ ቤት የሚቀርብበት ስነ-ስርዓትና ተያያዥ ጉዳዮች በረቂቅ ሕጉ ሊታዩ እንደሚገባ ምክረ ሃሳብ አቅርበዋል።
ረቂቅ ሕጉ በኢትዮጵያ የወንጀል ፍትህ አስተዳደር ውስጥ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ከሚውሉበት ሁኔታ ጀምሮ ፍርድ ቤት የሚቀርቡበት ጊዜና ተያያዥ ችግሮች ይፈታል የሚል እምነት እንዳላቸውም አክለዋል።
ዶክተር ዳንኤል አንድን ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር ከማዋል ጀምሮ በፍትህ ሂደት ሲያልፍ የተጠርጣሪ ሰዎችን ንጹህ ሆኖ የመገመት መብት መሰረት ያደረገ የሕግ ጥበቃ መኖር እንዳለበት ተናግረዋል።
በተለይ የዋስትና መብት የሚፈቀድበትና የሚከለከልበት ሁኔታ ተፈጻሚነቱ ላይ የስነ-ስርዓት ሕጉ እልባት ሊሰጥ እንደሚገባም ኮሚሽነሩ አስገንዝበዋል።