በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ፓርኮች ለጉዳት በመዳረጋቸው የዱር እንስሳት እየተመናመኑ ነው... ባለስልጣኑ - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ፓርኮች ለጉዳት በመዳረጋቸው የዱር እንስሳት እየተመናመኑ ነው... ባለስልጣኑ
አዲስ አበባ፤ታህሳስ 20/2013 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ የተለያዩ ፓርኮች ለጉዳት በመዳረጋቸው የዱር አንስሳት ላይ ችግር እየደረሰ መሆኑን የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ገለጸ።
በፓርኮች ጉዳት የባቢሌ ዝሆኖች፣ የአዋሽ ሳላዎችና የነጭ ሳር የሜዳ አህያዎች ቁጥር በየጊዜው እየተመናመነ መጥቷል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን መኮንን ለኢዜአ እንዳሉት በኦሮሚያ የሚገኙ ፓርኮች ለጉዳት እየተዳረጉ በመሆኑ የዱር እንስሳቱም ቁጥር እየተመናመነ መጥቷል።
በክልሉ አጎራባች ፓርኮች በነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክና ባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ ላይም ስጋት እንዳለ ጠቅሰዋል።
በፓርኮቹ የሚከናኑት ህገ ወጥ ሰፈራ፣ አደን፣ ከሰል ማክሰልና ልቅ ግጦሽ በብዝሃ ህይወት ላይ ጉዳት እያስከተለ ስለመሆኑም ተናግረዋል።
በአርሲ ዞን ከሚገኘው የሰንቀሌ ቆርኬዎች መጠለያ በስተቀር ቀሪዎቹ የክልሉ ፓርኮች ለጉዳት እየተዳረጉ መሆናቸውንም አቶ ሰለሞን ገልጸዋል።
የባቢሌ ዝሆኖች፣ የአዋሽ ፓርክ ሳላዎችና የነጭ ሳር የሜዳ አህያዎች ቁጥር በየጊዜው እየተመናመነ መጥቷል ነው ያሉት።
ያልተቀናጀ የልማት እንቅስቃሴ ሌላው ለፓርኮች ስጋት እንደሆነ ገልጸው፤ ለዚህም በመካከለኛው ስምጥ ሸለቆ አካባቢ በሚገኙ ሐይቆች የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ለብክለት እየተጋለጡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ሂደቱ ከቀጠለ ብርቅዬ የዱር እንስሳት 'ነበሩ ወደሚል ታሪክ' መቀየራቸው አይቀርም ሲሉም ስጋታቸውን አስቀምጠዋል።
በመሆኑም ከታሪክ ተወቃሽነት ለመዳን የፓርኮችን ብዝሃ ሕይወት መታደግና እንስሳቱንም መጠበቅ ይገባል ብለዋል።
በዚህም በማህበረሰብ ግንዛቤ ፈጠራ በመስራት በተለይም በሰንቀሌ ቆርኬዎች መጠለያ አባ-ገዳዎች ያላቸው ተሰሚነት ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዲስፋፋ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
በየደረጃው ያለ አመራር በፓርኮች አካባቢ የሚሰጡ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ታሳቢ በማድረግ የሕግ ማስከበር ስራውን እንዲያጠናክር አሳስበዋል።
በፓርኮች ላይ የሚደርሰውን ውድመት ለመታደግ በፓርኮች ውስጥና በአካባቢው የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎችን የኑሮ ዘይቤ መቀየር ያስፈልጋልም ብለዋል።
በዚህም ነዋሪዎችን ከቱሪዝም ተጠቃሚ በማድረግ የባለቤትነት ስሜት ኖሯቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል የትረስት ፈንድ ህግ ጸድቆ ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ ነው ብለዋል።
የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አቶ ከበደ ደሲሳ ችግሩ ከህዝብ ቁጥር መጨመር ጋር የተያያዘ እንጂ የህዝቡ ተፈጥሮን የመጠበቅ እሴት በመጥፋቱ አይደለም ይላሉ።
በተለይም በፓርኩ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች አማራጭ የገቢ ምንጭ ስለሌላቸው ለሕልውናቸው ሲሉ በፓርኮች በሚያደርጉት የግብርና እንቅስቃሴ ጉዳት እንደሚያደርሱ ገልጸዋል።
በመሆኑም ነዋሪዎች ከዘርፉ ተጠቃሚ የሚሆኑበትና ፓርኮችን ራሳቸው የሚጠብቁበትን ዕድል ለመፍጠር ይሰራል ብለዋል።
የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ግርማ፤ ሰዎችና ተፈጥሮ ሃብት አብረው መኖር እንደሚችሉ ገልጸው፤ ይህን ለማድረግ ግን የሰዎችን አዲስ የኑሮ ዘይቤ ይፈልጋል ብለዋል።
በፓርኮች ውስጥ በግብርና የሚተዳደሩ ሰዎችን ቀስ በቀስ ከግብርናው ይልቅ በቱሪስት አገልግሎት የገቢ ምንጭ እያገኙ የሚኖሩበትን የኑሮ አማራጭ ለመፍጠር ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።