የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የአንድነት ማዕከላት ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ

23
አዲስ አበባ ሀምሌ 14/2010 ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የአገር አንድነት ማዕከላት እንዲሆኑ ባዲስ መልክ እየሰራ መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ። ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌቴ እንዳሉት መንግስት ላለፉት አመታት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተፈጠሩ ችግሮችን ለመቀነስና ተቋማቱ አንድነትንና ልዩነትን ባግባቡ የተረዱ የኢትዮጵያዊነት ነፀብራቅ እንዲሆኑ እየሰራ ነው። በተቋማቱ እስካሁን ይነሱ የነበሩ ግጭቶችን መነሻ በማድረግ  ምክንያታቸውን በማጥናት ሊወሰዱ የሚገቡ መፍትሄዎችንም በማስቀመጥ ከተማሪዎች አመዳደብ እስከ ቦርድ አመራር ድረስ ባዲስ መልክ ለማዋቀር እየተሰራ መሆኑን ዶክተር ጥላዬ ገልጸዋል። እንደ ዶክተር ጥላዬ ገለጻ ከዚህ በተጨማሪም አገራዊ አንድነትንና ብሔራዊ መግባባትን በሚያጎለብት መንገድ በስነ ዜጋና ስነ ምግባር ትምህርትና በታሪክ ትምህርቶች ላይ ጥናት ተደርጎ የማሻሻያ ስራ ተሰርቷል። ይህም ተማሪዎቹ ከታች ጀምሮ ትክክለኛ የሃገራቸውን ታሪክ እንዲያውቁ፣ህብረ ብሄራዊነትን ተረድተው በአንድነት ለአገራቸው እንዲሰሩና የግጭት መነሻ መንስኤዎችን ለይቶ በማወቅ ቀድመው ነገሮችን ከተለያዩ እይታዎች አንጻር እንዲያመዛዝኑ ይረዳል ብለዋል። ለዚህም ምሁራኑ ለውጡን የሚያግዙና የሚያስቀጥሉ ዜጎችን ከማብቃት ረገድ ድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም