ቀጥታ፡

በ5 ወራት 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን መኪኖች የፈጣን መንገድ አገልግሎት አግኝተዋል-የኢትዮጵያ ክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ

አዲስ አበባ ታህሳስ 20/2013 (ኢዜአ) ባለፉት አምስት ወራት በአገሪቱ በሚገኙ ሁለት ፈጣን መንገዶች 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን መኪኖች አገልግሎት ማግኘታቸውን የኢትዮጵያ ክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ አስታውቋል፡፡

የኢንተርፕራይዙ የኮሚኒኬሽንና ማርኬቲንግ ቡድን መሪ ዛሃራ መሐመድ ለዥንዋ እንደተናገሩት በአዲስ -አዳማ 76 ኪሎ ሜትርና በድሬዳዋ-ዶሎ 220 ኪሎ  ሜትር ፈጣን  መንገድ  3 ነጥብ 6 ሚሊዮን መኪኖች አገልግሎት አግኝተዋል፡፡

በዚህም አገሪቱ 4 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ችላለች ብለዋል፡፡

ለ24 ሰዓት አገልግሎት የሚሰጡት ሁለቱ ፈጣን መንገዶች እየጨመረ የመጣውን የትራፊክ ፍሰት ለማስተናገድ የሚረዳ ቴክኖለጂ እንደ ተገጠመላቸው ተገልጿል፡፡

በምስራቅ አፍሪካም ሆነ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው የአዲስ-አዳማ ፈጣን  መንገድ  በኢትዮጵያ መንግስት በጀትና በቻይና መንግስት ድጋፍ ተገንብቶ እኤአ በ2014 ወደስራ መግባቱ ይታወቃል፡፡

የድሬዳዋ-ደወሌ ፈጣን መንገድ ደግሞ እ.አ.አ በሐምሌ ወር 2019 ነው አገልግሎት መስጠት የጀመረው፡፡

የቻይና ኢምፖርት ኤክስፖርት (ኤግዚም) ባንክ የድሬዳዋ-ዶሎ ፈጣን መንገድ ፕሮጀክት ወጪን 85 በመቶ ፋይናንስ ያደረገ ሲሆን ቀሪው 15 በመቶ በኢትዮጵያ መንግስት የተሸፈነ መሆኑን የቡድን መሪዋ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ የወጪና ገቢ ንግድ 95 በመቶ የሚንቀሳቀሰው በጅቡቲ ወደብ በኩል መሆኑን ተከትሎ የድሬዳዋ -ደወሌ ፈጣን መንገድ የንግድ  ልውውጡን በማሳለጥ  የአገሪቱን  ኢኮኖሚ  ለማሳደግ ጉልህ ሚና እያበረከተ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም