በአራተኛ ሣምንት ጨዋታዎች ጎንደር ከተማና ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸነፉ - ኢዜአ አማርኛ
በአራተኛ ሣምንት ጨዋታዎች ጎንደር ከተማና ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸነፉ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 20/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ አራተኛ ሣምንት ጨዋታዎች ጎንደር ከተማና ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸነፉ፡፡
በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የእጅ ኳስ ሜዳ በተካሄዱት ጨዋታዎች ጎንደር ከተማና ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል።
ጎንደር ከተማ ከምባታ ዱራሜን 24 ለ 21 እንዲሁም ቂርቆስ ክፍለ ከተማ አዲሱን የፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ ባህርዳር ከተማን 38 ለ 22 ረተዋል።
ትናንት በተደረገ የአራተኛ ሣምንት የሊጉ መርሃ ግብር ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ፌዴራል ማረሚያ ቤቶችን 33 ለ 31፤ ፌዴራል ፖሊስ ሚዛን አማን ከተማን 38 ለ 21 ማሸነፋቸው የሚታወስ ነው።
መከላከያ የአራተኛ ሣምንት የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ መርሃ ግብር አራፊ ክለብ ነው።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከልና መቆጣጠር ፕሮቶኮልን መሰረት ባደረገ መልኩ የፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታዎች በባህርዳር፣ በሐዋሳና በአዲስ አበባ ያለ ተመልካች እንዲካሄድ መወሰኑ ይታወቃል።
በዚሁ መሰረት የመጀመሪያዎቹ አራት ሣምንታት ጨዋታዎች በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም በሚገኘው የእጅ ኳስ ሜዳ ተከናውነዋል።
ከአምስተኛ እስከ ሰባተኛ ሣምንት ጨዋታዎች ከጥር 16 እስከ 23 ቀን 2013 ዓ.ም በሐዋሳ እንዲሁም የስምንተኛና የዘጠነኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከየካቲት 13 እስከ 26 ቀን 2013 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄዱ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።
በተመሳሳይ የሁለተኛው ዙር የፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታዎች በሦስቱም ከተሞች ይካሄዳሉ።
የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ መከላከያ በስድስት ነጥብ በግብ ክፍያ በልጦ በተመሳሳይ ስድስት ነጥብ ያላቸውን ቂርቆስና ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተሞችን አስከትሎ እየመራ ነው።
ቂርቆስና ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተሞች እርስ በእርስ ሲገናኙ ባሸነፈ በሚለው ሕግ በቅደም ተከተል ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።