በሶስት ክልሎች የተከሰተውን የበረሃ አንበጣ የመከላከል ስራ እየተሰራ ነው - ግብርና ሚኒሰቴር - ኢዜአ አማርኛ
በሶስት ክልሎች የተከሰተውን የበረሃ አንበጣ የመከላከል ስራ እየተሰራ ነው - ግብርና ሚኒሰቴር
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 20/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ በሶስት ክልሎች የተከሰተውን የበረሃ አንበጣ መንጋ ለመከላከል በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ግብርና ሚኒሰቴር ገለፀ።
መንጋው በሶማሌ ክልል ስድስት ዞኖች በሚገኙ 26 ወረዳዎች፣ በኦሮሚያ በባሌና በምስራቅ ባሌ ዞኖች ስድስት ወረዳዎች፣ በደቡብ ክልል ደግሞ በሐመር ወረዳ ተከስቷል።
የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አበራ ለማ ለኢዜአ እንዳስረዱት በእነዚህ ክልሎች በ134 ሺህ ሄክታር ላይ የተከሰተውን መንጋ ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ነው።
ከታሕሳስ መግቢያ አንስቶ ከሶማሌ ላንድ የገባው መንጋ በ246 ሺህ ሄክታር መሬት አሰሳ ተደርጎበታል ብለዋል።
መንጋውን ለመቆጣጠር በአውሮፕላን፣ ተሽከርካሪ ላይ በተገጠመ ሞተርና በሰው ኃይል ኬሚካል እየተረጨ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
የአንበጣ መንጋው በሰብል ላይ ጉዳት እንዳያደርስ በባሕላዊ ዘዴዎች ጭምር በመታገዝ የመከላከል ሥራው በመከናወን ላይ እንደሆነም አብራርተዋል።
መንጋው ወደ ሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች እንዳይስፋፋ አሰሳ እየተደረገ መሆኑንም አክለዋል።
በአገሪቷ ባለፈው ዓመት መጨረሻና በመስከረም 2013 ዓ.ም የተከሰተው የአንበጣ መንጋ በተቀናጀ እንቅስቃሴ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል።
የዓለም ምግብና እርሻ ድርጅት /ፋኦ/ መረጃ እንደሚያመለክተው የበረሃ አንበጣው በሶማሊያ፣ በኬንያ፣ በታንዛንያና በኢትዮጵያ ታይቷል።
በቀይ ባህር ዳርቻዎች፣ በሳዑዲ ዓረቢያ፣ በኤርትራና በሱዳን ጠረፎች እንቁላል እየጣለ በመራባት ላይም ነው።
ይህ መንጋ ወደ ኢትዮጵያና ኬንያ እየገባ በመሆኑ ጥንቃቄ እንዲደረግም ድርጅቱ አስጠንቅቋል።