ቀጥታ፡

የ''ገበታ ለአገር'' ፕሮጀክት አገራዊ አንድነትና ብሔራዊ መግባባት በመፍጠር ጉልህ ሚና አለው

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 20/2013 (ኢዜአ) የ''ገበታ ለአገር'' ፕሮጀክት አገራዊ አንድነትና ብሔራዊ መግባባት በመፍጠር ረገድ ሚናው የጎላ እንደሆነ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የመንግስት ሠራተኞች ገለፁ።

የኢትዮጵያን የቱሪስት መዳረሻነት ለማሳደግ እየተከናወኑ ከሚገኙ ተግባራት መካከል የገበታ ለአገር ፕሮጀክት ይገኝበታል።

ፕሮጀክቱ በጎርጎራ፣ በወንጪና በኮይሻ አካባቢዎች የተፈጥሮ መስህቦች ላይ መሰረት አድርጎ  ዘመናዊና ማራኪ የቱሪዝም መዳረሻዎች የሚገነቡበት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ "ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ለኢትዮጵያ ብልጽግና አሻራቸውን የሚያኖሩበት" ብለውታል ፕሮጀክቱን ይፋ ሲያደርጉ።

ይህን ተከትሎ የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብሮች ተዘጋጅተው ባለሃብቶች፣ የንግዱ ማኅበረሰብና ሌሎችም ለፕሮጀክቱ ድጋፍ በማድረግ እየተሳተፉበት ይገኛሉ።

የመንግስት ሠራተኞችም በራሳቸው ተነሳሽነት ከደመወዛቸው ተቆራጭ በማድረግ በፕሮጀክቱ አሻራቸውን ለማሳረፍ ተንቀሳቅሰዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ሠራተኞች ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ከሚያስገኘው ጥቅም ተቋዳሽ ለመሆን ዛሬ ላይ አስተዋጽኦ ማበርከት ይገባል ይላሉ።

የገበታ ለአገር ፕሮጀክት በዋናነት አገራዊ አንድነትና ብሔራዊ መግባባትን በማጎልበት ረገድ ጉልህ ሚና እንዳለውም ተናግረዋል።

የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሠራተኛው አቶ አበበ ጥላሁን ፕሮጀክቶቹ የመንግስት ወይም የአካባቢው ማኅበረሰብ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ናቸው ነው ያሉት። 

የኑሮ ሁኔታው አስቸጋሪ ቢሆንም ካለው ላይ ቀንሶ አሻራውን በማኖር የባለቤትነት ስሜት ለመፍጠር አስተዋጽኦ ማበርከት ያሻል ባይ ናቸው።

አቶ ጥላሁን መሰለ የሠራተኛና ማኅበራዊ ሚኒስቴር ሠራተኛ ናቸው 'ገበታ' የሚለው ስያሜ በራሱ መሰባሰብንና በአንድ ላይ መመገብን የሚያመለክትና ቱባውን ኢትዮጵያዊ ባሕል የሚያጎላ ነው ብለዋል።

በፕሮጀክቱ በመሳተፋቸው መደሰታቸውን ገልፀው ሕዝብን ከሕዝብ ከማቀራረብ ባሻገር ለትውልዱ የአገር ፍቅርን በተግባር ለማሳየት እንደሚያስችል ገልፀዋል።

ፕሮጀክቱ በዜጎች መካከል ልዩነት ለመፍጠር የሚሰሩ አካላት ዓላማቸው እንደማይሳካና ዜጎች በአገራዊ ጉዳይ ሁሌም እጅ ለእጅ እንደሚያያዙ የታየበት ነው ያሉት ደግሞ አቶ አንተነህ ጸጋዬ ከትምህርት ሚኒስቴር ናቸው።

ለገበታ ለአገር ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ ከአዲስ አበባ አስተዳደርና ከከተማዋ ባለሃብቶች በድምሩ 390 ሚሊዮን ብር መሰባሰቡን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የመንግስትና የግል ተቋማትም ለፕሮጀክቱ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ላይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም