በሲዳማ ክልል ለ40 ግንባር ቀደም ግብር ከፋዮች እውቅና ተሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል ለ40 ግንባር ቀደም ግብር ከፋዮች እውቅና ተሰጠ

ሐዋሳ፣ ታኀሳስ 19/2013 (ኢዜአ) የሲዳማ ክልል ገቢዎች ባለሥልጣን ለመጀመሪያ ጊዜ ለ40 ግንባር ቀደም ግብር ከፋዮች ዛሬ እውቅና ሰጠ።
ከክልሉ ሁሉም ዞኖች ለተወጣጡ ለእነዚህ ግብር ከፋዮች በሀዋሳ ከተማ በተዘጋጀው የእውቅና አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት ከርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ እጅ የምስክር ወረቀትና ዋንጫ ተሸልመዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንዳሉት ግብር ከፋዩ ህብረተሰብ የሚጠበቅበትን ግዴታ በአግባቡ በመወጣት ከድህነት ጋር የሚደረገውን ትግል በማገዝ የበኩሉን ሚና ሊጫወት ይገባል።
ግብርና ታክስ የሚከፈለው ለሰፊው ህዝብና ለጋራ ዓላማ ማስፈጸሚያ በመሆኑ በዚህ ረገድ ተሸላሚዎች የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ ብለዋል።
በተለይ ሲዳማ ክልል አዲስ እንደመሆኑ በህዝቡ ዘንድ ሰፊ የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ እንዲቻል ለግንባር ቀደም ግብር ከፋዮች የሚሰጠው እውቅና እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
በሥነ-ሥርዓቱ የተገኙት የገቢዎች ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ምህረት ምናስብ ሲዳማ ክልል በአዲስነት ከመመስረቱ ጋር ተያይዞ ግብር ከፋዮች ከማደራጀትና ወደ ስራ ከመግባት አልፎ በታማኝነት ለህግ ተገዢ የሆኑ ግብር ከፋዮች እውቅና መስጠቱን አድንቀዋል።
የዛሬ ተሸላሚ ግብር ከፋዮች በአርአያነታቸው በመቀጠል ሌሎችም ግብር ከፋዮች ለህግ ተገዢ በመሆን እንዲከተሏቸው በቁርጠኝነት እንዲሰሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የሲዳማ ክልል ገቢዎች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሙሉወርቅ ደረሰ በበኩላቸው የመንግሥት ግብርን በታማኝነት የከፈሉትን ማበረታታት ተገቢነት ያለውና ተጠናክሮ የሚቀጥል ነው ብለዋል።
የዛሬ ተሸላሚዎች ግዴታቸውን መወጣታቸው ለህዝብ ያላቸውን ተቋርቋሪነት የሚያሳይ በመሆኑ ተሳትፏቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
በክልሉ በበጀት ዓመቱ ሶስት ቢሊዮን 300 ሚሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ በመጀመሪያዎቹ አምስት ወራት አንድ ቢሊዮን 500 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን ገልጸዋል።
ገቢው ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ620 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ እንዳለው ጠቅሰዋል።
ከተሸላሚዎች መካከል አስመጪና ላኪ አቶ ደገፋ ስሜ በሰጡት አስተያየት በ2012 በጀት ዓመት የሚጠበቅባቸውን 18 ሚሊየን ብር ግብር በወቅቱ በመክፈል ከክልሉ ግብር ከፋዮች አንደኛ ወጥተው ዋንጫ መሸለማቸውን አስታወሰው ይህም ለበለጠ ሥራ እንዳነሳሳቸው ተናግረዋል።