ከአዳማ ከተማና አካባቢዋ የተውጣጡ ከ2ሺህ በላይ ወጣቶች በዝዋይ ሃይቅ ላይ እንቦጭ የማስወገድ ዘመቻ አካሄዱ - ኢዜአ አማርኛ
ከአዳማ ከተማና አካባቢዋ የተውጣጡ ከ2ሺህ በላይ ወጣቶች በዝዋይ ሃይቅ ላይ እንቦጭ የማስወገድ ዘመቻ አካሄዱ
አዳማ፣ ታህሳስ 19 ቀን 2013 (ኢዜአ) ከአዳማ ከተማና አካባቢዋ የተውጣጡ ከ2ሺህ በላይ ወጣቶች በዝዋይ ሃይቅ ላይ ዛሬ እንቦጭ የማስወገድ ዘመቻ ላይ ተሳትፈዋል።
በምሥራቅ ሸዋ ዞን በሚገኙት የቆቃና ዝዋይ ሃይቆች የእንቦጭ አረም የማስወገድ ዘመቻ መጀመሩን የዞኑ ዋና አስተዳደር አቶ አላካ ሲንብሩ አስታውሰዋል።
ዋና አስተዳዳሪው በተለይ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ከ3ሺህ ሄክታር በላይ የቆቃና የዝዋይ ሃይቆች በእንቦጭ አረም ተወረዋል።
አረሙ በተለይ ሉሜ፣ ቦራ፣ ዱግዳና አዳሚ ቱሉ ወረዳዎች የሚገኘውን የሁለቱን ሃይቆች የውሃ ክፍል መሸፈኑን አስታውቀዋል።
ሃይቆቹን ለመታደግ ዘመቻ መጀመሩንና በሶስት ምዕራፍ ተከፍሎ እየተከናወነ መሆኑን አመልክተው፤ በመጀመሪያው ምዕራፍ 970 ሄክታር ላይ የሚገኝ እንቦጭ የማስወገድ ሥራ እንደሚከናወን ገልጸዋል።
ሃይቆቹን ለመታደግ በዞን ደረጃ እቅድ ወጥቶ የዞኑን ህብረተሰብ በማሳተፍ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የዞኑ የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ፋጡማ ሁሴን እንደገለፁት፤ ሃይቆቹን የወረረውን የእንቦጭ አረም ለማስወገድ ከዘመቻ ባለፈ በሳይንሳዊ መንገድ በጥናት የተደገፈ ዘላቂ እልባት ለመስጠት እየተሰራ ነው።
“ከኦሮሚያ ክልልና ከፌዴራል መንግስት ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራን ነው” ብለዋል።
የአዳማ ከተማ አስተዳደር የብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ አለማየሁ ቱሉ በበኩላቸው “አስተዳደሩ እንቦጭን ከሁለቱ ሃይቆች ለማስወገድ ከዞኑ 750 ሄክታር የውሃ ክፍል በመረከብ ዛሬ የማስወገድ ዘመቻ ተጀምሯል” ብለዋል።
ዛሬ በዝዋይ ሃይቅ ላይ በተጀመረው ዘመቻ ከ2 ሺህ 100 በላይ ወጣቶች መሳተፋቸውን ገልጸዋል።
ዘመቻው ለአንድ ወር እንደሚቆይ ጠቁመው፤ በየደረጃው የሚገኙ የወጣት አደረጃጀቶችን በማሳተፍ አረሙን ለማስወገድ መታቀዱን ተናግረዋል።
በዛሬው ዘመቻ እስከ 10 ሄክታር የእንቦጭ አረም ለማንሳት ወጣቱ በቦታው መገኘቱን አስረድተዋል።
የአዳማ ከተማ አስተዳደር ወጣቶች ሊግ ሊቀመንበር ታዬ ተሊላ በተለያዩ የወጣት አደረጃጀቶች ሥር የሚገኙ ከ27 ሺህ በላይ ወጣቶች በዘመቻው እንደሚሳተፉ ጠቁሟል።
ዛሬ በተጀመረው ዘመቻ ከስድስት ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ የወጣቶች ሊግ፣ ማህበርና የፌዴሬሽን አባላት መሳተፋቸውን ጠቅሷል።