ቀጥታ፡

የዳኞችና ታዛቢዎች ማህበር ከእግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ሊነጋገር ነው

አዲስ አበባ ግንቦት 1/2010 የኢትዮጵያ ዳኞችና ታዛቢዎች ማህበር ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ለመነጋገር ነገ ጠቅላላ ጉባኤ መጥራቱን ገለጸ። እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ሚያዚያ 25 ቀን 2010 ዓ.ም ለመገናኛ ብዙሀን በላከው መግለጫ ከዳኞች ማህበር ጋር ሚያዚያ 28 ቀን 2010 ዓ.ም ስብሰባ እንደሚያደርግ ገልጾ ነበር። ነገር ግን ማህበሩ የስብሰባውን ጉዳይ ለመወሰን የማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ መሰብሰብ እንዳለበትና አሁን የማህበሩ አባላት የሆኑ ዳኞች በየሚኖሩበት ስፍራ ስለሚገኙ ጠቅላላ ጉባኤው መሟላት እንደማይችል ለፌዴሬሽኑ ማሳወቁ የሚታወስ ነው። በተጨማሪም የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ሚያዚያ 29 እና 30 ቀን 2010 ዓ.ም በስፖርታዊ ጨዋነት ዙሪያ በአዳማ በተካሄደው ስብስባ የማህበሩ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ተሳትፈዋል። በተጠቀሱት ምክንያቶች ማህበሩ ከፌዴሬሽኑ ጋር ስብሰባ ማድረግ የሚችለው ግንቦት 4 ቀን 2010 ዓ.ም እንደሆነ ማህበሩ ለእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ በጻፈው ደብዳቤ ገልጾ ነበር። ይሁንና ክለቦች ውድድሩ በመቋረጡ ምክንያት ለአላስፈላጊ የበጀት ወጪ እንደሚዳረጉና በዝግጅታቸው ላይ ተጽእኖ እያሳደረ መሆኑን በመገንዘብ ማህበሩ ግንቦት 4 ቀን 2010 ዓ.ም ከፌዴሬሽኑ ጋር ሊያደርግ የነበረውን ውይይት ነገ እንዲሆን መወሰኑን የኢትዮጵያ የዳኞችና ታዛቢዎች ማህበር ገልጿል። የማህበሩ ፕሬዝዳንት ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ትግል ግዛው ለኢዜአ እንዳሉት ከእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ጋር የሚያደርገው ውይይት የኢትዮጵያ ዳኞችና ታዛቢዎች ማህበር ሚያዚያ 24 ቀን 2010 ዓ.ም ባደረገው ጠቅላላ ጉባዔ ባወጣው ባለ 10 ነጥብ የአቋም መግለጫ የተመሰረተ ነው። ማህበሩ ለዳኞች እንዲሟሉ ባቀረበው ጥያቄዎች ዙሪያ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የስራ ሃላፊዎች ምላሽ ይሰጣሉ ብለዋል። ፌዴሬሽኑ ባቀረበው ማብራሪያ ላይ በመመስረት የማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ ዳኞች ወደ ውድድር ይመለሱ ወይስ አይመለሱ? ለሚለው ጉዳይ ውሳኔ እንደሚሰጥ ነው ፕሬዝዳንቱ ያስረዱት። "ማህበሩ ውድድሮች ተቋርጠው ክለቦችና የስፖርት ቤተሰቡ እንዲጎዱ ምንም አይነት ፍላጎት የለውም፤ ያቀረብናቸው ጥያቄዎች ምላሽ ካገኙ ወደ ውድድር በፍጥነት እንመለሳለን" ሲሉ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ትግል ግዛው ገልጸዋል። የኢትዮጵያ የዳኞችና ታዛቢዎች ማህበር ሚያዚያ 24 ቀን 2010 ዓ.ም ባደረገው ጠቅላላ ጉባዔ ባወጣው ባለ 10 ነጥብ የአቋም መግለጫ ዳኞች ለሶስት ሳምንት ያህል ማንኛውንም አይነት ውድድር እንደማይዳኙ መግለጻቸው ይታወቃል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም