ቀጥታ፡

'ገበታ ለአገር'' ፕሮጀክት አገራዊ የአንድነት ስሜት ፈጥሯል - የቀድሞ ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ሮማን ተስፋዬ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 19/2013 (ኢዜአ) የገበታ ለአገር ፕሮጀክት እንደ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ አገራዊ የአንድነት ስሜት መፍጠሩን የሀይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ሮማን ተስፋዬ ገለጹ።

ኢትዮጵያ በቱሪዝም ሃብቷ ከአፍሪካ ግንባር ቀደም ከሆኑ አገራት አንዷ ብትሆንም ከዘርፉ የሚጠበቀውን ያህል ጥቅም እያገኘች አይደለም።

የቱሪስት መዳረሻዎችን በሚፈለገው ልክ ማስተዋወቅና ማልማት አለመቻሏ ደግሞ ለዘርፉ መቀጨጭ በምክንያትነት ይጠቀሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ዘርፉ እንዲያንሰራራ ያደርጋል ያሉትን "ገበታ ለአገር" የተሰኘ ፕሮጀክት ይፋ ማድረጋቸው ይታወቃል።

በዚህም ትኩረት ተነፍጎት የቆየው የአገሪቷን የተፈጥሮ ሀብት የማልማት ስራ በጎርጎራ፣ በኮይሻና በወንጪ አካባቢዎች ለመስራት ታቅዶ በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል።

ኢዜአ በአካባቢ ጥበቃና ኢኮ ቱሪዝም ላይ የሚሰራውን በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝና በባለቤታቸው የተመሰረተውን የሀይለማሪያምና ሮማን ፋውንዴሽን ዋና ስራ አስፈፃሚን አነጋግሯል።

የፋውንዴሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ የቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ሮማን ተስፋዬ በአገሪቷ በተፈጥሮ ብቻ የተገኙ በርካታ ድንቅ የቱሪስት መስህብ ስፍራዎች መኖራቸውን ይናገራሉ።

እነዚህ የተፈጥሮ የቱሪስት መስህብ ስፍራዎች ታሪካዊ አሻራ ያረፈባቸው፣ እምቅ ሀብትና ቅርሶችን ጭምር የያዙ በመሆናቸው እንደ "ገበታ ለአገር" አይነት ፕሮጀክቶች መጠናከር አለባቸው ይላሉ።

ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷ ብቻ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገቢ ስለሚያመጣ ሀብቱን ጥቅም ላይ በማዋል  ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻልም አንስተዋል።

እንደ "ገበታ ለአገር" ያሉ ፕሮጀክቶችን አቅም በፈቀደ መጠን ማስፋት እንደሚገባና ሕዝቡም ለዚህ ድንቅ ዓላማ ድጋፍ በማድረግ የሚሳተፍበት መሆን እንዳለበት ነው የተናገሩት።

ወይዘሮ ሮማን የ"ገበታ ለአገር" ፕሮጀክት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የፈጠረውን አይነት አገራዊ የአንድነት ስሜት መፍጠሩንም ገልፀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ባለፈው ዓመት መጨረሻ በኦሮሚያ ወንጪ፣ በአማራ ጎርጎራና በደቡብ ኮይሻን ለማልማት "ገበታ ለአገር" የተሰኘ ፕሮጀክት ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም