ለጉዳት የተጋለጠውን የመካከለኛው ስምጥ ሸለቆ ንዑስ ተፋሰስ የቱሪዝም ፀጋዎች ወደ አገልግሎት መቀየር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ለጉዳት የተጋለጠውን የመካከለኛው ስምጥ ሸለቆ ንዑስ ተፋሰስ የቱሪዝም ፀጋዎች ወደ አገልግሎት መቀየር ይገባል
ታህሳስ 19/2013 (ኢዜአ) በተፈጥራዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች ለጉዳት የተጋለጠውን የመካከለኛው ስምጥ ሸለቆ ንዑስ ተፋሰስ የቱሪዝም ፀጋዎች በማልማት ወደ አገልግሎት መቀየር እንደሚገባ በተፋሰሱ ላይ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች አመለከቱ።
በመካከለኛው ስምጥ ሸለቆ አካባቢ ዘላቂነት ያለው የቱሪዝም መዳረሻ ለማልማት የጋራ ግብረ ሐይል ተቋቁሟል።
ማዕከላዊ ስምጥ ሸለቆ ከ14 ሺህ 400 በላይ ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን ይህም ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ ተፋሰስ 27 በመቶውን ይሸፍናል።
የማዕከላዊ ስምጥ ሸለቆ ቱሪዝምን ዘላቂነት ማረጋገጥ ላይ ያተኮረ አገራዊ መድረክ በሻሸመኔ ከተማ ተካሂዷል።
በመካከለኛው ስምጥ ሸለቆ ቱሪዝም መስህብነት አቅም ላይ ጥናት ያደረጉት አቶ አብዱራህማን ቁብሳና አቶ ዋሪዮ ኩኖ ለኢዜአ አንደገለጹት ተፈጥሯዊ ቦታዎች፣ ፓርኮች፣ ሐይቆች፣ ብርቅዬ አዕዋፍትና አጥቢ የዱር እንስሳት እንዳለው፤ ይህም ለቱሪዝም የሚውል ከፍተኛ ሀብት እንዳለው ይገልጻሉ።
የአብጃታ ሻላ፣ ላንጋኖ፣ ዝዋይና ሌሎች ሐይቆችና የበርካታ ብዝሃ ሕይወት ባለቤት የሆነው የመካከለኛው ስምጥ ሸለቆ አካባቢ ለአዲስ አበባና ለሌሎች የኢኮኖሚ ማዕከላት ከተሞች ያለው ቅርበት ደግሞ ሌላው ዕድል መሆኑን ይገልጻሉ።
አካባቢውን በሚያቋርጡ መንገዶች መተሳሰሩ፣ በሆቴል መሰረተ ልማት ተደራሽነትና በበርካታ አቅጣጫ የሚገናኝ ቦታ መሆኑ ለአገር ውስጥና ለውጭ ቱሪዝም መዳረሻነት ሌላው ዕድል እንደሆነም ጠቁመዋል።
በአጠቃላይ አካባቢው በተፈጥሯዊ ገፅታው፣ ባለው የእንስሳት ሀብትና ሐይቆች ለተፈጥሮ ቱሪዝም ዕምቅ አቅም እንዳለው ተናግረዋል።
መካከለኛው ስምጥ ሸለቆ ለቱሪዝም መዳረሻነት እምቅ አቅም ቢኖረውም ቅሉ የአካባቢ ጥበቃ ስራ ባለመሰራቱ የንዑስ ተፋሰሱ ስነ-ምህዳር እየተጎዳና ፀጋዎቹም እየተጎሳቆሉ መሆኑን ባለሙያዎቹ ያነሳሉ።
ለአብነትም በሕገወጥ ሰፈራ ፓርኮች እየወደሙ፣ የዱር እንስሳት እየተመናመኑ መምጣታቸውን፣ የሐይቆች መጠን የመቀነስና የመበከል ስጋቶች መደቀናቸውን እንዲሁም የሐይቆች አካባቢ የመሬት ቅርምት እንደሚስተዋል ጠቁመዋል።
በመሆኑም ስምጥ ሸለቆውን በመጠበቅ ለተፈለገው የቱሪዝም አገልግሎት በማዋል ከዘርፉ መጠቀም እንደሚገባ አብራርተዋል።
የኦሮሚያ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ከበደ ደሲሳ ከክልሉ የቱሪዝም ፀጋዎች መካከል ማዕከላዊ ስምጥ ሸለቆ አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ ስፍራው የክልሉን 80 በመቶ ሐይቆች የሚሸፍን፣ የዱር እንስሳት፣ ፓርኮችን፣ ባህላዊና ታሪካዊ ቦታቸውን ያቀፈ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
የቢሮ ኃላፊው የአካባቢውን ፀጋዎች በማልማትና በማስተዋወቅ ዘላቂ ቱሪዝም ለመገንባት ትኩረት ሳይሰጠው በመቆየቱ ንዑስ ተፋሰሱ ለጉዳት ስለመዳረጉም ያምናሉ።
እንደ አገር ለቱሪዝም ዘርፍ የተሰጠውን ትኩረት መነሻ በማድረግ ትኩረት ሳይሰጠው በቆየው ስምጥ ሸለቆ መዳረሻዎች ማልማትና ማስተዋወቅ ላይ ስራዎች መጀመራቸውን ተናግረዋል።
በሰው ሰራሽ ችግሮች ብዝሃ ሕይወቱ የተጎዳውን የማዕከላዊ ስምጥ ሸለቆ በማልማትና በማስተዋወቅ የአካባቢውን ማኅበረሰብ በስራ ዕድልና በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
ይሁንና በአንድ ተቋም ብቻ መስራት ውጤት የሚያስገኝ ባለመሆኑ መንግስት ከግል ድርጅቶች ጋር እንደሚሰራ ገልፀዋል።
የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ግርማ ቱሪዝም ለኢትዮጵያ ቅንጦት ሳይሆን የሕልውና ጉዳይ መሆኑን፤ ከምጣኔ ሃብታዊ ፋይዳው ባሻገር ማኅበረሰባዊ ትስስርና ትውውቅ የሚፈጠርበት ወሳኝ ዘርፍ ነው ይላሉ።
በቱሪዝም ኢትዮጵያ በርካታ የመዳረሻ ስፍራዎች ማልማትና ማስተዋወቅ ስራዎችን መጀመሩን ገልጸው፤ ከነዚህም መካከል እምቅ የቱሪዝም ፀጋዎች ያለው መካከለኛው ስምጥ ሸለቆ አንዱ ነው ብለዋል።
የመካከለኛው ስምጥ ሸለቆ ከደረሰበት ሰው ሰራሽና ተፈጥራዊ ጉዳት እንዲያገግም ብሎም ፀጋዎቹን ማልማት በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።
በዚህም በስምጥ ሸለቆ አካባቢ ዘላቂነት ያለው የቱሪዝም ልማትና መዳረሻ ለመገንባት የጋራ ግብረ ሐይል መቋቋሙን አክለዋል።
ይህም በኦሮሚያ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ሰብሳቢነት የፌዴራልና የክልል ባለድርሻ ተቋማትና ግብረሰናይ ድርጅቶች የተካተቱበት ነው።