በወምበራ ወረዳ የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል ሊገነባ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በወምበራ ወረዳ የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል ሊገነባ ነው
አሶሳ ታህሳስ 19 / 2013 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ወምበራ ወረዳ የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል ሊገነባ መሆኑን የክልሉ ስፖርት ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ወምበራ ወረዳ ታዋቂዋ አትሌት አልማዝ አያና ተወልዳ ያደገችበት አካባቢ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡
በኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ መሃመድ ዓሊ ለኢዜአ እንደገለጹት ማሰልጠኛ ማዕከሉ የሚገነባው በመተከል ዞን ወምበራ ወረዳ ጥንታዊ ከተማ በሆነችው ደብረዘይት ነው፡፡
የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከሉ በ14 ሄክታር መሬት ላይ እንደሚያርፍ ተናግረዋል፡፡
ማሰልጠኛ ማዕከሉ ደረጃውን የጠበቀ የአትሌቲክስ መሮጫ መም ያለው ስታዲየምን ጨምሮ የስልጠና ማዕከላተ ፣ መዝናኛ ቦታዎች እና ሌሎችንም መገልገያዎች እንደሚያካትት አስረድተዋል፡፡
ማዕከሉ በወምበራ እንዲሆን የተመረጠው የአካባቢው አየር እና መልክዓ ምድር ለአትሌቲክስ ስፖርት ምቹ መሆኑ በጥናት በመረጋገጡ እንደሆነ ባለሙያው ገልጸዋል፡፡
የግንባታ ወጪ በመንግስት እና ህዝብ የሚሸፈን ነው ብለዋል፡፡
ግንባታውን ለማስጀመር ሃብት አሰባሳቢ እና የቴክኒክ ኮሚቴ መዋቀሩንና በተያዘው ሳምንት ስራ እንደሚጀምሩ አመልክተዋል፡፡
ከሀብት አሰባሰቡ በተጓዳኝ ግንባታው ዘንድሮ እንደሚጀመር ይጠበቃል።
በመተከል ዞን ወምበራ ወረዳ በአትሌቲክስ ስፖርት ኢትዮጵያን ለዓለም ያስተዋወቀችው አትሌት አልማዝ አያና ተወልዳ ያደገችበት አካባቢ እንደሆነ ተመልክቷል።