በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጎጂ ልማዳዊ ደርጊቶችና ኢ-ፍትሐዊነትን በጋራ ልንታገል ይገባል- የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ

89

ታህሳስ 19 / 2013 (ኢዜአ) በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጎጂ ልማዳዊ ደርጊቶችና ኢ-ፍትሐዊነትን በጋራ ልንታገል ይገባል ሲሉ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ገለጹ።

በደቡብ ኦሞ ዞን ሴቶችን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ የተዘጋጀ የንቅናቄ መድረክ በጅንካ ከተማ እየተካሄደ ነው።

መድረኩ የኃይለማሪያምና ሮማን ፋውንዴሽን ከፊንላንድ ኢምባሲ በተገኘ ድጋፍ የተዘጋጀ ነው።

በመድረኩ ላይ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው፣ የፌዴራል፣ የክልልና የዞን አመራሮችን ጨምሮ በኢትዮጵያ የፊንላንድ አምባሳደር ኦውቲ ሆሎፓይነንና ባለቤታቸው ተገኝተዋል።

የመድረኩ ዓላማ ሴቶች ከወንዶች እኩል በልማት ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ህብረተሰቡ በባለቤትነትና በግንባር ቀደምነት እንዲንቀሳቀስ ንቅናቄ መፍጠር እንደሆነ ተገልጿል።

የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ከበደ ሳህሌ፤ፋውንዴሽኑ በዞኑ ያለውን የመልማት ክፍተቶች ለመሙላትና የዞኑ ሴቶች በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ፕሮጀክት ቀርፆ ሊሰራ በመምጣቱ ምስጋና ችረዋል።

ፋውንዴሽኑ በዞኑ በትህምርት፣ ጤናና አካባቢ ጥበቃ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ለሚያከናውናቸው ተግባራትም የዞኑ መስተዳድር ሙሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አለሚቱ ዑሞድ በበኩላቸው ሴቶችን የኢኮኖሚ አቅም ለመገንባት ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

የሃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን በተለይም በአርብቶ አደር አካባቢዎች የሴቶችን ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ ያለውን እንቅስቃሴ አድንቀዋል።

የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው፤ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር የህዝቦችን ህይወት እንዲሻሻልና እንዲለወጥ በፋውንዴሽናቸው እያከናወኑት ላለው ተግባር  አመስግነዋቸዋል።

በዚህም በሴቶችና ህጻናት፣ በአካባቢ ጥበቃና በስራ እድል ፈጠራ የሚከናወኑት ተግባራት የክልሉን ልማትያግዛሉ ብለዋል።

የክልሉ መንግስትም ፋውንዴሽኑ የህዝቦች ህይወት እንዲሻሻል የሚያደርገውን ጥረት እንደሚደገፍ አረጋግጠዋል።

የፋውንዴሽኑ የቦርድ ሊቀመንበር የቀድሞው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ፣ የህልውና የጀርባ አጥንት የሆኑ ሴቶችን ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች አላቆ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ሴቶች በባህል፣ በሃይማኖትና ማህበረሰባዊ መስኮች ወደፊት ጎልተው እንዳይወጡ የሚያደርጉ የአስተሳሰብ ችግሮች በመፍታት ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።

በሴቶች ላይ የሚታየውን ኢ- ፍትሐዊነት፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ለመፍታት ሁሉም ድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም