በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተቋቋመው ግብረ ኃይል የመተከል ዞንን የፀጥታ ማስከበር ስራ ተረከበ - ኢዜአ አማርኛ
በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተቋቋመው ግብረ ኃይል የመተከል ዞንን የፀጥታ ማስከበር ስራ ተረከበ
ታህሳስ 19/ 2013 (ኢዜአ) በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የተቋቋመው ግብረ ኃይል የመተከል ዞንን የፀጥታ ማስከበር ስራ መረከቡን ሌፍተናንት ጄኔራል አስራት ዴኔሮ አስታወቁ።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተቋቋመውና ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና የመከላከያ ሠራዊት አመራሮች የተካተቱበት ግብረ ኃይል በዞኑ የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ስራውን ሙሉ በሙሉ ጀምሯል።
የፀጥታ ኃይሉን የሚመሩት ሌፍተናንት ጄኔራል አስራት ዴኔሮ እንደገለጹት፤ የንፁሃንን ሕይወት በማጥፋት ወንጀል የተሳተፉ ተጠርጣሪዎችን የማደን ስራው ቀጥሏል።
“በወንጀሉ የተሳተፉ ተጠርጣሪዎች በአጭር ጊዜ የሕግ ተጠያቂ ይሆናሉ” ሲሉም ተናግረዋል።
ችግሩን ከመሰረቱ ለመፍታት በአሁኑ ወቅት በየደረጃው ከሚገኙ የማኅበረሰብ አባላትና አመራሮች ጋር ውይይት እየተካሄደ ሲሆን ወንጀለኞቹን በመለየት ለሕግ የማቅረቡ ስራም እንደሚቀጥል ሌፍተናንት ጄኔራሉ ተናግረዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን የተፈናቀሉትን መልሶ የማቋቋምና የሕዝቡን የዕለት ተዕለት ኑሮ ቀድሞ ወደ ነበረበት የመመለስ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።
ሌፍተናንት ጄኔራል አስራት ዴኔሮ “በመተከል ዞን የተጀመረው የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ተልዕኮ በአጭር ጊዜ ይጠናቀቃል” ብለዋል።