በአገር ግንባታና በብሔራዊ መግባባት ላይ የሚጠበቅብንን እንወጣለን ... የታሪክ ምሑራንና ፀሐፊያን - ኢዜአ አማርኛ
በአገር ግንባታና በብሔራዊ መግባባት ላይ የሚጠበቅብንን እንወጣለን ... የታሪክ ምሑራንና ፀሐፊያን
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 18/2013(ኢዜአ) በአገር ግንባታና በብሔራዊ መግባባት ላይ የሚጠበቅባቸውን ሚና ሙያዊ ስነ-ምግባርን በተላበሰ መልኩ ለመወጣት ማኅበራቸውን ዳግም ለመመስረት መስማማታቸውን የታሪክ ምሑራንና ፀሐፊያን አስታወቁ።
የታሪክ ምሑራንና ፀሐፊያኑ ይህን ያስታወቁት ለአራት ቀናት በቢሾፍቱ ባካሄዱት የምክክር መድረክ ማጠቀለያ ነው።
የምክክር መድረኩ በሠላም ሚኒስቴር አስተባባሪነት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የማኅበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ ጋር በመተባበር እየተካሄደ የሚገኘው የብሔራዊ የማኅበረሰብ ተኮር የምክክር መድረክ አካል ነው።
የታሪክ ምሑራንና ፀሐፊያኑ ከምክክራቸው በኋላ 'የታሪክ ባለሙያዎች የቢሾፍቱ ስምምነት 2013' በሚል ባለ አራት ነጥብ የጋራ ስምምነት አውጥተዋል።
"እንደ ዕውቀት ማኅበረሰብ ተቀራርበን ለመስራት ተስማምተናል" ያሉባቸውን ነጥቦችም አስቀምጠዋል።
የታሪክ ሙያ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚመጡበትን ጫናና ተፅዕኖዎች በመቋቋም በሁሉም የአገሪቷ ክፍሎች የተሳሳቱ የታሪክ ትርክቶችን ለማረምና በአሳማኝ የታሪክ ማስረጃዎች ላይ የተመሰረቱ ሕትመቶችን ለማውጣት ስምምነት መድረሳቸውን አስታውቀዋል።
ለዚህም ተቋርጦ የቆየውን የታሪክ ባለሙያዎች ማኅበር ዳግም በመመስረት ማንቀሳቀስ አንደኛው እርምጃ መሆኑ ተመልክቷል።
በሌላ በኩል በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስተባባሪነት ተዘጋጅቶና ተተችቶ በየካቲት 2012 ዓ.ም የፀደቀው የኢትዮጵያና የአፍሪካ ቀንድ ታሪክ ኮመን ኮርስ ተግባራዊ ያልሆነበትን ምክንያት ተቋሙን በመጠየቅ የተዘጋጀው ሞጁል ለዩኒቨርሲቲዎች እንዲሰራጭና ትምህርቱ የሚጀመርበት ሁኔታ እንዲመቻች እንሰራለን ብለዋል።
በታሪክ ትምህርትና በፖለቲካ መካከል ያለውን ጤናማ ትስስር ለማዳበር፣ ፖለቲከኞች በታሪክ ትምህርት ላይ የሚያሳድሩትን ጤናማ ያልሆነ ጫና ለማስተካከልና ችግሩን በሂደት ለመፍታት ተከታታይ ውይይት እናካሂዳለን ነው ያሉት የታሪክ ምሑራኑና ፀሐፊያኑ።
ከዚህ ቀደም የተሰሩ ስራዎችን ለማጠናከርና በምክክር መድረኩ ስምምነት የተደረሰባቸውን ውሳኔዎች ተፈጻሚ ለማድረግም 12 አስተባባሪዎችን ሰይመዋል።
በዴስቲኒ ኢትዮጵያ አመቻችነት ከሀሴት የሳይኮ ቴራፒ ማዕከል ጋር በመተባበር በተካሄደው የምክክር መድረክ 60 የኢትዮጵያ የታሪክ ምሑራንና የታሪክ ፀሐፊያን ተሳትፈዋል፡፡