በኢሉአባቦራ ዞን በ3 ሺህ 570 ማህበር ለተደራጁ ወጣቶች የስራ እድል ተፈጠረ

64
መቱ ሀምሌ 14/2010 በኢሉአባቦራ ዞን በተጠናቀቀው የበጀት አመት በማህበር ለተደራጁ ከ57 ሺህ ለሚበልጡ ወጣቶች የስራ እድል መፈጠሩን የዞኑ ስራ እድል ፈጠራና የከተማ ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት ገለጸ። በጽህፈት ቤቱ የእቅድ ባለሙያ አቶ ሰለሞን አስረስ እንዳሉት የስራ እድሉ የተፈጠረው በከተማና በገጠር በ3 ሺህ 570 ማህበራት ለተደራጁ ወጣቶች ነው። ወጣቶቹ በግብርና፣ እንስሳት ማድለብ፣ የማዕድን ልማት፣ ንግድ፣ አገልግሎት፣ የእንጨትና ብረታ ብረት ስራ መሰማራታቸውን ገልጸዋል። በተሰማሩበት የስራ መስክ ውጤታማ እንዲሆኑ ከ93 ሚሊዮን ብር በላይ ብድርና 2 ሺ 558 ሄክታር በላይ መሬት መከፋፈሉን ጠቁመዋል። በዞኑ ቡሬ ወረዳ ቶሊ ጬካ ቀበሌ ከአስር ጓደኞቹ ጋር በእርሻ ስራ የተሰማራው ወጣት ኦብሳ አራርሶ በሰጠው አስተያየት ማህበራቸው በተረከበው 20 ሄክታር መሬት በዘንድሮ የመኸር ወቅት በተለያየ የሰብል ዘር የመሸፈን ስራ በመከናወን ላይ መሆኑን ገልጿል። መንግስት ከእርሻ መሬት በተጨማሪ የእርሻ ትራክተርና ምርጥ ዘር በብድር በማቅረብ ድጋፍ ማድረጉን የሚናገረው ወጣቱ ማህበራቸው ገበያ ተኮር ሰብሎችን በስፋት በማምረት ተጠቃሚ ለመሆን እየሰራ መሆኑን ተናግሯል፡፡ በተመሳሳይ ሙያ የተሰማራው ወጣት ረታ ሙለታ በበኩሉ ከዚህ ቀደም የሌሎችን አርሶ አደሮች ማሳ በእኩል በማረስ ኑሮውን ሲገፋ ቆይቷል። ዘንድሮ ግን እሱን ጨምሮ ለ10 ወጣቶች የእርሻ መሬት በመሰጠቱ ሰርተው ለመለወጥ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ገልጿል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም