ቀጥታ፡

የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የአፈጻጸም ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ ተገለጸ

ባህርዳር፤ታህሳስ 18/2013(ኢዜአ) የአካል ጉዳተኞችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የሚስተዋሉ የአፈጻጸም ችግሮች ለመፍታት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ ገለጹ።

በዓለም ለ29ኛና በኢትዮጵያ ለ28ኛ ጊዜ ለተታይ ሁለት ቀናት በተለያዩ ዝግጅቶች በባህርዳር ከተማ የተከበረው የአካል ጉዳተኞች ቀን ዛሬ ተጠናቋል።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በማጠናቀቂያው ላይ ተገኝተው እንደገለጹት በማን ላይ መቼ እንደሚያጋጥም በማይታወቀው የአካል ጉዳተኝነት አማካኝነት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለማቃለል የመንግስትና የህዝብ ሚና ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ነው።

“ለአካል ጉዳተኞች የምናደርገው ነገር ሁሉ ችሮታ ሳይሆን ህገ መንግስታዊ የመብት ድንጋጌዎችን የመፈጸም ግዴታ መሆኑን በመገንዘብ የሚስተወሉ የአመለካከት፣ የአስተሳሰብና አግላይነትን ማስወገድ ይገባል” ብለዋል ።

“ከልማትና ከኢኮኖሚ ተሳትፎ በመገደብ ሀገርን ማሳደግና ማበልጸግ የማይቻል በመሆኑ በየስራ መስኩ የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሁላችንም ሃላፊነት ነው” ሲሉም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ምህረት ንጉሴ በበኩላቸው በዓለም ላይ ከሚገኙ አንድ ቢሊዮን የአካል ጉዳተኞች ውስጥ 80 በመቶ የሚሆኑት በታዳጊ አገራት ይገኛሉ።

በኢትዮጵያም ከአጠቃላይ ህዝቡ ከ20 ሚሊዮን በላይ የሚሆነው የአካል ጉዳት ያለበት መሆኑን ጠቁመው፤ አሁን ላይ ኮሮና ባስከተለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የበለጠ ጉዳት የደረሰበት የህብረተሰብ ክፍል መሆኑንም ጠቁመዋል።

አሁን ላይ ባለው የኮቪድ 19 ወቅትና በመጪው ጊዜ ለአካል ጉዳተኞች የጋራ አቅምን በመጠቀም የጤናና ማህበራዊ እንክብካቤ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

በፌዴራል ሆስፒታሎች ውስጥ የአካል ጉዳተኛ ማዕከላትን በማቋቋም፣ አገልግሎት የሚሰጥ የሰለጠነ የሰው ሃይል በመመደብና ቁሳቁስ በማሟላት እየተሰራ እንደሚገኝ የገለጹት ደግሞ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ናቸው።

በቀጣይም የተቋቋሙት ማዕካላት ያስገኙትን ውጤትና ያመጡትን ለውጥ በመገምገም ወደ ሌሎች ክልሎችና ጤና ተቋማት ለማስፋት እንደሚሰራ አስገንዝበዋል።

ከሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበርም የአካልና የህክምና ተሃድሶ አገልግሎቶች በአገሪቱ እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመው “ይህም ሁለንተናዊ የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ነው”ብለዋል።

የኢፌዴሪ ሰራተኛና ማህበራዊ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንዳሉት በኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚስተዋለውን የተዛባ አመለካከት ሰብሮ መውጣት ያስፈልጋል።

ይህም የተጎጂነት አስተሳሰብን በማስወገድ እምቅ አቅማቸውን ለሀገር ልማትና ብልጽግና ለማዋል የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

“አካል ጉዳተኞችን አካታች፣ ምቹና ዘላቂ የተሻለ አለምን በድህረ ኮቪድ-19 እንገንባ” በሚል መሪ ቃል በተከበረው በዓል ላይ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም