ቀጥታ፡

የኦሮሚያ ስፖርት አካዳሚ ግንባታ እስከ ሰኔ ወር ድረስ እንዲጠናቀቅ ክልሉ እገዛ ያደርጋል

ሱሉልታ፤ ታህሳስ 18/2013(ኢዜአ) በሱሉልታ ከተማ በግንባታ ላይ የሚገኘው የስፖርት አካዳሚ እስከ መጪው ሰኔ ወር ድረስ እንዲጠናቀቅ ክልሉ እገዛ ያደርጋል ሲሉ በኦሮሚያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ አዲሱ አረጋ ገለጹ።

አቶ አዲሱ አረጋና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉን ጨምሮ የስፖርት ቤተሰቦች የአካዳሚውን የግንባታ ሂደት ጎብኝተዋል።

በዚህ ወቅት አቶ አዲሱ ግንባታው ከአራት ዓመት በላይ ያስቆጠረው አካዳሚው 13 የስፖርት አይነቶችን ማሰልጠን የሚያስችልና በአገሪቷም ቀዳሚ መሆኑን  ተናግረዋል።

በ800 ሚሊዮን ብር ወጪ እየተከናወነ የሚገኘው የአካዳሚው ግንባታ ሲጠናቀቅ 160 ስፖርተኞችን ተቀብሎ ማሰልጠን ያስችላል ብለዋል።

እንደ አቶ አዲሱ ገለጻ አካዳሚው ለክልሉም ሆነ ለአገሪቷ በርካታ ስፖርተኞችን ለማፍራት ትልቅ ዕድል የሚፈጥር ነው።

በመሆኑም የግንባታው ሂደት በፍጥነት እንዲጠናቀቅ የክልሉ መንግሥት ስራውን በትኩረትና በቅርበት የሚያግዝ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አትሌት ደራርቱ ቱሉ መሰል ዘመናዊ የስፖርት ማዘውተሪያዎች ስለሚኖራቸው ጠቀሜታ አውስታለች።

የአካዳሚው ግንባታ በርካታ ጠቃሚ ነገሮችን ያካተተ ቢሆንም የተሟላ እንዲሆን ዘንድ ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም መገንባት እንዳለበትም አመልክታለች።

አትሌት ስለሺ ስህን እና አሰልጣኝ ሁሴን ሼቦ በበኩላቸው የአካዳሚው መገንባት የተሻሉ ስፖርተኞችን ለማፍራት ትልቅ ዕድል የሚሰጥ መሆኑን መስክረዋል።

ይህን መሰል አካዳሚዎችን በሌሎች አገራት መመልከታቸውን ገልጸው፤ በአካዳሚው መገንባት መደሰታቸውን ተናግረዋል።

ግንባታውን የሚያከናውነው የስራ ተቋራጭ ድርጅት ዋና ተቆጣጣሪ መሐንዲስ አቶ ኢሳያስ ኪዳኔ ስራውን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል። የተጠናቀቁ፣ በግንባታ ላይ የሚገኙ እንዲሁም በንድፍ ስራ ላይ ያሉ የአካዳሚውን ስራዎች በማስረዳት።

አካዳሚው የመማሪያና የአስተዳደር ሕንጻዎች፣ የአሰልጣኞችና ሰልጣኞች መኖሪያ እንዲሁም የስፖርት ማዘውተሪያዎችን ያካተተ ነው።

ክልሉ በጉጂ አካባቢ ያስገነባው የስፖርት አካዳሚ ተጠናቆ ወደ ሥራ መግባቱና በገላን፣ በለገጣፎ፣ በሰበታና በጊንጪ አካባቢዎችም የስፖርት ማዘውተሪያዎች እያስገነባ መሆኑም ተገልጿል።

ከጉብኝቱ በኋላም በኦሮሚያ ክልል እየተካሄደ ያለው የጋራ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ አካል የሆነው የቡድን ስፖርታዊ እንቅስቃሴም ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም