ቀጥታ፡

የምስራቅ ወለጋ ዞን ነዋሪዎች ወንጀለኞችን ለማደን የተሰማሩ የጸጥታ አካላትን ሰብል ሰበሰቡ

ነቀምቴ፤ታህሳስ 18/2013(ኢዜአ) የምስራቅ ወለጋ ዞን ነዋሪዎች ወንጀለኞችን ለማደን ለተሰማሩ የጸጥታ አካላትና ቤተሰቦች የደረሱ ሰብሎችን በመሰብሰብ ድጋፍ ማድረጋቸውን የዞኑ ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደረጀ አበራ ገለጹ።

ነዋሪዎቹ ለመከላከያ ሠራዊት ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አድርገዋል።

ምክትል ዋና አስተዳዳሪው ለኢዜአ እንዳታስወቁት ነዋሪው ሰላም ማስከበር ላይ የሚገኙ 1ሺህ 147 የፀጥታ አባላት የሆነ 221 ሄክታር መሬት ላይ የሚገኝ የደረሰ ሰብል በመሰብሰብ ድጋፍ አድርጓል።

በምርት አሰባሰቡ ላይ 6ሺህ 792 ሰዎች መሰማራታቸውን የተናገሩት አቶ ደረጀ፣ የሕብረተሰቡ ተሳትፎ በገንዘብ ሲተመን ወደ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ መሆኑንም ተናግረዋል።

የሐሮ ሊሙ ወረዳ የአስተዳደርና የፀጥታ ጽህፈት ቤት የሚሊሻ ዘርፍ የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ፍቃዱ ኦልጅራ በበኩላቸው የወረዳው ሕዝብ በሰላም ማስከበር ስራ ላይ ለተሰማሩ የሚሊሻ አባላት 44ሺህ 185 ብር ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።

ነዋሪው ከዚህ ባለፈ ለአካባቢው ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ለሚከናወኑ ስራዎች አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን በተግባር እንዳሳየም ጠቁመዋል።

የኪረሙ ወረዳ የለሊስቱ ሶምቦ ቀበሌ ነዋሪ ሚሊሻ ለሜሣ ሁሉቃ በሰጡት አስተያየት እሳቸው ከአገር መከላከያና ከኦሮሚያ ልዩ ኃይል ጋር በመተባበር የወረዳውን ሰላም በማስከበር ላይ ይገኛሉ።

ይሄንን በማድረጋቸው በሳቸውም ሆነ በቤተሰባቸው ህይወት ላይ የኢኮኖሚ ተጽዕኖ እንዳይገጥማቸው የወረዳው ሕዝብ በ5 ሄክታር መሬት ላይ ያለሙትን ሰብል ስለሰበሰቡላቸው መደሰታቸውን አስረድተዋል።

የዚሁ ወረዳ የጨፌ ጉዲና ቀበሌ ነዋሪ ሚሊሻ ፍቃዱ አከሣ የሰላም ማስከበር ላይ መሰማራታቸውን አስረድተው ህዝቡ በ6 ሄክታር መሬት ላይ የዘሩትን የዳጉሳ፣ የጤፍ፣ የበቆሎ፣ እና የኑግ ሰብል ሙሉ በሙሉ እንደሰበሰበላቸው አስታውቀዋል።

የዞኑ ነዋሪዎች ከአካባቢ ሰላም ማስከበር ባለፈ በግንባር የጁንታውን ቡድን ላስወገደው የሃገር መከላከያ ሰራዊት ያላቸውን አጋርነት እያሳዩ መሆኑን የዞኑ ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደረጀ አበራ አስረድተዋል።

የሕወሐት ጁንታ ቡድን በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመውን ጥቃት በማውገዝ ወደ 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ድጋፍ ማድረጋቸውንም ምክትል ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል።

ሕዝቡ ካደረገው ድጋፍ ውስጥም 2ሚሊዮን 560 ሺህ ብር ግምት ያላቸው 128 ሰንጋዎች የሚገኙበት ሲሆን ቀሪው በጥሬ ገንዘብ የተበረከተ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም