ቀጥታ፡

በጁንታው መወገድ እንደ ሁለተኛ ዜጋ የምንቆጠርበት ምዕራፍ ተዘግቷል ... የኮረም ከተማ ነዋሪዎች

ሰቆጣ፤ታህሳስ 18/2013(ኢዜአ)''በጁንታው ቡድን ተወልደን ባደግንበት ሃገር እንደ ሁለተኛ ዜጋ ስንቆጠር የነበረበት የጊዜ ምዕራፍ ተዘግቶ መብታችን ተከብሮ በነፃነት መኖር ጀምረናል'' ሲሉ የኮረም ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ።

የኮረም ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች ለሀገር መከላከለያ ሰራዊት፣ለአማራ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ አባላት በህግ ማስከበር ዘመቻው ለከፈሉት መስዋትነት ምስጋና ያቀረቡበትን ሰላማዊ ሰልፍ ዛሬ አካሂደዋል።

ነዋሪዎቹ ባካሄዱት ሰልፍ "በህወሀት ጁንታ እንደ ሁለተኛ ዜጋ የምንቆጠርበት የጊዜ ምእራፍ አብቅቷል፤ ነጻ ላወጡን ሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ኅይልና ሚሊሻ አባላት ምስጋና እናቀርባለን " ሲሉ ድጋፋቸውን ገልጸዋል።

ከሰልፈኞቹ መካከል አቶ አስፋው ሃደሩ ለኢዜአ እንደገለጹት የህወሃት ጁንታ ይህ ቀረው የማይባል አሰቃቂ በደልና መከራ ሲፈጽምባቸው ቆይቷል።

"የጁንታው ቡድን ባላፉት 30 ዓመት በአፍ መፍቻችን አማርኛ ቋንቋ ፍርድ ቤትም ሆነ በሌሎች ተቋማት እንዳንጠቀም ከልክሎን ቆይቷል" ብለዋል።

"የማንነት ጥያቄዎችን የሚያነሱ ዜጎች ለእስራትና ግድያ ሲዳረጉ ቆይተዋል" ያሉት አቶ አስፋው፤ የህወሃት ጁንታ ለግል ጥቅሙ ካልሆነ በስተቀር የዜጎችን በፈለጉትና በፈቀዱት ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ጠብቆ እንደማያውቅ አስታውሰዋል።

"የጁንታው የሃይልና የአፈሙዝ አገዛዝ ባልታሰበና ባልተጠበቀ መንገድ ተቋጭቷል" ያሉት ደግሞ መምህር ሲሳይ ዘውዴ ናቸው።

"የህወሃት ቡድን ህዝብን በማስጨነቅና በማሸበር ሰላም ሲነሳ የቆየ ስብእና የሌለው ስብስብ ነው" ብለዋል።

የኦፍላ ህዝብ በቡድኑ ለአፈናና ጭቆና ተዳርጎ መቆየቱን ጠቁመው ልጆቻቸው በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዳይማሩ ተከልክለው እንደነበርም ተናግረው፤ "አሁን ላይ የመጣው ለውጥ ለኮረምና አካባቢው ህዝብ ዳግም እንደ መወለድ ነው" ብለዋል አቶ ሲሳይ።  

"የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነትና በመተባበር የእናት ጡት ነካሹን ጁንታ አሳፍሯል" ያሉት ደግሞ የኮረም ከተማ ጊዜያዊ ከንቲባ አቶ ሙሉጌታ ካሴ ናቸው።

ቡድኑ ባለፉት 30 ዓመት የዘረጋውን  የውሸት ፌደራሊዝም ተገን በማድረግ የህዝቦችን መብት በመጣስ የአካባቢውን የተፈጥሮ ሃብት ሲዘርፍ መቆየቱን አስታውሰው፤ "ጁንታው በለኮሰው እሳት አይቀጡ ቅጣት ተቀጥቶ ዳግም እንዳይነሳ ወድቆ ቀርቷል" ብለዋል።

አሁን ላይ በአካቢው ሰላማዊ ሁኔታ ያለ ቢሆንም የህወሃት የጥፋት ቡድን ርዝራዥ ቅሪቶች ሰርገው  በመግባት ጉዳት እንዳያደርሱ ህብረተሰቡ በንቃት ሰላሙን መጠበቅ እንዳለበትም አሳስበዋል።

የሃገር መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ አባላት የህወሃት ጁንታን ለማስወገድ ለከፈሉት መስእዋትነት በትውልድ ዘንድ ሲዘከሩ ይኖራሉ" ሲሉ ጊዜያዊ ከንቲባው አስታውቀዋል።

በኮረም ከተማ የተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ባለ አራት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት የተጠናቀቀ ሲሆን በሰቆጣ ከተማም ተመሳሳይ ህዝባዊ ሰልፍ በዛሬው እለት ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም