የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አካታች ህግ ከማውጣት ጀምሮ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ... ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አካታች ህግ ከማውጣት ጀምሮ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ... ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር

ባህር ዳር፣ ታህሳስ 18/2013(ኢዜአ) መንግስት የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አካታች የሆነ ህግ ከማውጣት ጀምሮ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
"አካል ጉዳተኞችን አካታች፣ ምቹና ዘላቂ የተሻለ ዓለምን በድህረ ኮቪድ-19 እንገንባ" በሚል መሪ ሃሳብ ሀገር አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን በባህር ዳር ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው።
በአለም አቀፍ ደረጃ ለ29ኛ ጊዜ፣ በኢትዮጵያ ለ28ኛ ጊዜ በተከበረው የአካል ጉዳተኞች ቀን መድረክ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንዳሉት መንግስት የአካል ጉዳተኞችን ጥያቄ ለመመለስ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው።
"ከዚህ ቀደም አካል ጉዳተኞችን የሚያካትት አስገዳጅ የህግ ማዕቀፍ ስላልነበረ አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ የሚሰሩ ስራዎች ከቦታ ቦታ ዥንጉርጉር እንዲሆኑ አድርጎ ቆይቷል" ብለዋል።
"አሁን ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ደረጃ ጀምሮ ለአካል ጉዳተኞች ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው"ያሉት ሚኒስትሯ አካታች የሆነ የአካል ጉዳተኞች ህግ ወጥቶ ተግባራዊ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል ።

ህጉ በዚህ አመት ተጠናቆ ፈጣን ተግባራዊ ምላሾች እንዲሰጡ ሚኒስትሯ አስታውቀዋል።
በርካታ አካል ጉዳተኞች በየደረጃው የሚገጥሟቸውን ችግሮችን ተቋቁመው በማለፍ ለሃገራቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ እንደሆነም ገልጸዋል።
"የአካል ጉዳተኞች ተጠቃሚነት" የሚለውን ሃሳብ "የአካል ጉዳተኞች ጠቃሚነት" ወደ ሚል በመቀየር ለሃገርና ህዝብ እያበረከቱ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ መቀጠል አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።
''አሁን እንደ ሀገር ትልቁ ችግር የአካል ጉዳተኝነት ሳይሆን ልበ ስውርነትና ከሰውነት በታች ማሰብ ነው'' ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሙሉነሽ አበበ ናቸው።

በኢትዮጵያም ሆነ በአለም ላይ ሙሉ አካል አለኝ ከሚል የተሻለ ፋና ወጊ ተግባራት እያከናወኑ ያሉ የአካል ጉዳተኞች መኖራቸውን ገልፀዋል።
የአካል ጉዳተኞች ችግሮችን ተቋቁመው እራሳቸውንና ሃገራቸውን የሚጠቅም ስራ እያከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።
እንደ አማራ ክልል ለሌሎች ክልሎች ተሞክሮ የሚሆን አካል ጉዳተኞችን አካቶ የሚያበረታታ አሰራር መዘርጋቱን አመልክተዋል።
በአሁኑ ሰዓት እንደ ሃገር ለአካል ጉዳተኞች የተሻለ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ ናቸው።

"የሚቀሩ ስራዎች ቢኖሩም በተለይ የአካል ጉዳተኞችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማሳደግ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች የሚያበረታቱና ከዚህ ቀደም ያልነበሩ ናቸው" ብለዋል።
6ኛውን አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የመጀመሪያውን ድርሻ በሚይዘው የምርጫ ማስፈጸሚያ ደንብ አካል ጉዳተኞችን ያካተተ እንዲሆን በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቅሰዋል።
"ያለ እኛ ስለ እኛ አትስሩ" የሚለውን የአካል ጉዳተኞች መርህ መንግሰት በመቀበል ህጎች ሲረቀቁ አካል ጉዳተኞች ተሳታፊ እንዲሆኑ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
በምክክር መድረኩ ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ ሚኒስትሮች፣የክልል ቢሮ ኅላፊዎችና የአካል ጉዳተኞች ማህበራት አመራሮች ተሳትፈዋል።