ቀጥታ፡

የወጣት አደረጃጀቶች ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ እንዲውል የ10 ሚሊዮን 800ሺህ ብር ቦንድ ገዙ

ባህር ዳር፣  ታህሳስ 17/2013 (ኢዜአ) በአማራ ክልል የወጣት አደረጃጀቶች ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ እንዲውል የ10 ሚሊዮን 800ሺህ ብር የቦንድ ግዥ ማከናወናቸውን የክልሉ ወጣቶች ማህበራት ፌዴሬሽን አስታወቀ። 

የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ወጣት ኃይለሚካኤል ካሳሁን ለኢዜአ እንደገለጸው፤በክልሉ የወጣት አደረጃጀቶች ውስጥ የታቀፉ አባላት  ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ሃብት የማሰባሰብ ስራ በንቅናቄ ሲያከናወኑ ቆይተዋል።

በዚህም ባለፉት አምስት ወራት ውስጥ  የ10 ሚሊዮን 800ሺህ ብር የቦንድ ግዥ ማከናወናቸውን  አስታውቋል።


በተካሄደው የቦንድ ግዥ ንቅናቄም አራት ሺህ 237 ወጣቶች ቦንድ በመግዛት መሳተፋቸውን የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ተናግሯል።

በቀጣይም አባላት ተጨማሪ የቦንድ ግዥ እንዲፈጽሙ የቅስቀሳ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጿል።

በክልሉ የሚገኙ ወጣቶች የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ አንስቶ በቦንድ ግዥ፣ ተፋሰስ ልማት፣ ችግኝ ተከላና እንክብካቤ ስራ ግንባር ቀደም ሆነው እየተሳተፉ እንደሚገኙም ተመልክቷል።

በዋግህምራ ዞን የሰቆጣ ከተማ ነዋሪ ወጣት ፍቅሬ ደረጀ በሰጠው አስተያየት ፤ በቦንድ ግዥ ንቅናቄው የ500 ብር ግዥ መፈፀሙን ተናግሯል።

ቀደም ሲልም የአንድ ሺህ ብር ግዥ መፈጸሙን አሰታውሶ ፤ በቀጣይም ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚጠበቅበትን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።

በባህር ዳር ከተማ የሚኖረው ወጣት ዘላለም ታከለ እንዳለው  ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ድጋፍ እንዲውል  የአንድ ሺህ ብር የቦንድ ግዥ አከናውኗል።

በጣና ኃይቅ ላይ የተከሰተውና ለህዳሴ ግድብ ስጋት የሆነው የእንቦጭ  አረምን ከማስወገድ ባለፈ በተፋሰሱ በሚካሄደው የችግኝ ተከላና እንክብካቤ ስራም እየተሳተፈ መሆኑን ጠቅሷል።

በአማራ ክልል ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ የወጣት አደረጃጀቶች ከ1 ሚሊዮን 600ሺህ የሚበልጡ አባላት እንዳሏቸውም ከፌዴሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም