ባለስልጣኑ ለቡና ቅምሻ፣ የላቦራቶሪና የዘመናዊ ባሬስታ ማሰልጠኛነት ያዘጋጀውን ማዕከል አስመረቀ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 17/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን በ50 ሚሊዮን ዩሮ ያዘጋጀውን የቡና ቅምሻ፣ የላቦራቶሪና የዘመናዊ ባሬስታ ማሰልጠኛ ማዕከል አስመረቀ።

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተወከሉ አባላትን ጨምሮ የግብርና ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ማዕከሉን መርቀው የከፈቱት የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን "ባለስልጣኑ ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ የኢትዮጵያን ቡና ለዓለም ገበያ ለማስተዋወቅ እያደረገ ያለው ጥረት መቀጠል አለበት" ብለዋል።

የባለስልጣኑ አዲስ መተግበሪያ ጥሩ አጋዥ እንደሚሆን ጠቁመው፤ አሰራሩ ጊዜ ቆጣቢ ከመሆኑ ባለፈ በዓለም ገበያ ተፎካካሪ ለመሆን ያለው ጠቀሜታ የጎላ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

ከማሰልጠኛ ማዕከሉ በተጨማሪ ዛሬ ለምረቃ የበቃው ሶፍትዌር ቡና ላኪ፣ አምራችና ተቀባዩን የሚያስተሳስር አዲስ ቴክኖሎጂ ከመሆኑ በላይ ድካምን፣ ወጪንና ጊዜን የሚቆጥብ መሆኑንም አንስተዋል።

"በግብርና ሚኒስቴር በኩል አርሶ አደሩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ ምርቱ በዓለም ገበያ ተፈላጊ እንዲሆን የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል" ሲሉም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ የተመረቀው አዲስ መተግበሪያ በቡና ምርት ግብይት ውስጥ ያሉ የተለያዩ ህገ ወጥ አሰራሮችን እንደሚያስቀር ጠቁመዋል፡፡

"መተግበሪያው ቡና ከመነሻ ጀምሮ እስከ ማዕከል ድረስ ያለውን ሂደት በየቦታው ባሉ ጣቢያዎች አማካኝነት ለመከታተል ያስችላል" ብለዋል።

በተለይ ለቡና ላኪዎች ከብሔራዊ ባንክና ከጉምሩክ ጋር ያላቸውን ምልልስ በማስቀረት ቀልጣፋ አሰራር ለመዘርጋት እንደሚያስችል ገልፀዋል።

500 ሺህ ብር ወጪ የተደረገበት መተግበሪያው ከቡና ግብይት ጋር በተያያዘ ከተለያዩ ተቋማት ጋር ፈጣንና ተአማኒ መረጃዎችን በቀላሉ ለመቀያየር ያስችላል ተብሏል።

የቡና ቅምሻ፣ የላቦራቶሪና የዘመናዊ ባሬስታ ማሰልጠኛ ማዕከል ግብዓት እየተሟላለት እንደሆነ ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በማዕከሉ የተለያዩ አገልግሎቶች የሚሰጡባቸው ከ10 በላይ ክፍሎች መዘጋጀታቸውን ገልጸው፤ ማዕከሉ ከመጪው ሚያዚያ ወር ጀምሮ ሰልጣኞችን በመቀበል እንደሚጀምርም ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም