ቀጥታ፡

ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ቅበላ አቅሙን በአምስት እጥፍ እንደሚያሳድግ አስታወቀ

ጋምቤላ፣ ታህሳስ 17/2013(ኢዜአ) ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ አሁን ያሉትን ከአምስት ሺህ 800 በላይ የተማሪዎች ቁጥር በአምስት እጥፍ እንደሚያሳድግ አስታወቀ።

ዩኒቨርሲቲው ያዘጋጀው የአስር ዓመታት መሪ እቅድ በባለድርሻ አካላት አስገምግሟል።

በግምገማው መድረክ የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዘዳንት ዶክተር ከተማ ጥላሁን እንዳሉት በቀጣይ አስር ዓመታት የዩኒቨርሲቲውን የቅበላ አቅም ከማሳዳግ በተጓዳኝ ለምርምር ዘርፍም ትኩረት ሰጥቷል።

በተለይም በመደበኛና ተከታታይ ትምህርት አሁን ላይ ያሉትን ከአምስት ሺህ 800 በላይ ተማሪዎች በቀጣይ አስር ዓመታት በአምስት እጥፍ ለማሳደግ ማቀዳቸውን አስታውቀዋል።

የትምህርት ፕሮግራሞቹንም ከ31 ወደ 62 እንደሚያድግ የገለጹት ዶክተር ከተማ ከመጀመሪያና ሁለተኛ ድግሪ በተጨማሪ በሶስተኛ ዲግሪም ሥልጠና የመጀመር እቅድ እንዳላቸው አስረድተዋል።

ከመማር ማስተማር ስራው በተጓዳኝ በተለይም በክልሉ ያለውን የግብርና፣ ማዕድን ፣ ቱሪዝምና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶችን በምርምር በማገዝ በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል ጭምር ይሰራል ብለዋል።

በግምገማ መድረክ ከተሳተፉ ባለድርሻ አካላት መካከል አቶ ኡቦንግ ኡቻላ በሰጡት አስተያየት ዩኒቨርሲቲው ክልሉ የሚያስፈልገውን የሰው ኃይል ታሳቢ ያደረገ ስልጠና ሊሰጥ ይገባል ብለዋል ።

በክልሉ በተለይም በጤናውና ትምህርት ዘርፍ ከፍተኛ የሆነ የሠለጠና የሰው ኃይል እጥረት እንዳለ ጠቁመው ተቋሙ በነዚህ ዘርፎች ስልጠና ቢጀመር መልካም መሆኑን ተናግረዋል።

በክልል በከፍተኛ ደረጃ እየተመናመነ ያለውን የተፈጥሮ ደን በመታደግ ረገድ ዩኒቨርሲቲው ሊሰራ እንደሚገባ ያመለከቱት ደግሞ ሌላው ተሳታፊ አቶ ቶማስ የማሎ ናችው።

አቶ ፒተር ጋርኮት በበኩላቸው በክልሉ ያለውን የእንስሳት ጤና ባለሙያ ችግር ለመፍታት ዩኒቨርሲቲው በዘርፉ ሥልጠና እንዲጀምር አስተያየት ሰጥተዋል።

የዩንቨርሲቲው የስራ ኃላፊዎች የተሳታፊዎቹን አስተያየቶች እቅዱን ለማዳበር እንደሚጠቀሙበት በሰጡት ማብራሪያ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም